Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች 259 ሚሊየን ብር የአይነት ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በደቡብ ኦሞ ዞን በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች 259 ሚሊየን ብር ግምት ያለው የምግብ ድጋፍ አድርጓል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈፃሚ አሸብር ባልቻ እንዳሉት ድጋፉ በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች፣ ኛንጋቶም፣ ሐመርና ሳላማጎ ወረዳዎች በድርቅና ተያያዥ ችግሮች ለተጎዱ የማህበረሰብ ክፍሎች የተደረገ ነው።

ድጋፉ 26 ሺህ 225 ኩንታል የበቆሎ ዱቄት፣ 679 ኩንታል አልሚ ምግብ፣ 13 ሺህ 112 ኩንታል ባቄላ እና 87 ሺህ 418 ሊትር ዘይትን ያካተተ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ድጋፉ በወረዳዎቹ ለሚገኙ ከ140 ሺህ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎች ተደራሽ የሚደረግ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

ከምግብ ድጋፍ ባሻገር በአካበቢው ድርቅን ለመቋቋምና የአርብቶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚከናወኑ የመስኖ ልማት ስራዎችን ለመደገፍ 20 የውሃ መሳቢያ ፓምፖች ድጋፍ መደረጉንም ስራ አስፈፃሚው አመልክተዋል።

ተቋሙ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በማሰብ ካለው አቅም ላይ በማካፈል ያደረገው የሰብአዊ ድጋፍ መሆኑን ጠቅሰው ድጋፉ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር አማካኝነት እንደሚሰራጭም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ቦርድ ሰብሳቢ አበራ ቶላ በበኩላቸው ማህበሩ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በኩል የተደረገውን ድጋፍ ለተጎጂዎች ተደራሽ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።

በዞኑ ወደ 400 ሺህ የሚጠጉ የማህበረሰብ ክፍሎች በድርቅና ተያያዥ ችግሮች ሳቢያ ለምግብ እጥረት መጋለጣቸው ተጠቁሟል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.