Fana: At a Speed of Life!

የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት መርሐ ግብርን ውጤታማ ለማድረግ በትኩረት መሥራት እንደሚጠበቅ ተመለከተ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት መርሐ ግብር ውጤታማ እንዲሆን በልዩ ትኩረት መስራት እንደሚገባ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የ2015 በጀት ዓመት የከተማ ልማት ሴፍቲኔትና ስራ ፕሮጀክት አፈጻጸም እየተገመገመ ነው፡፡

በሚኒስቴሩ የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ÷ በመርሐ ግብሩ በርካቶችን ተጠቃሚ ማድረግ ቢቻልም ከችግሩ ስፋት አንጻር አሁንም ብዙ መስራት እንደሚጠበቅ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

ሚኒስቴሩ ከፌደራልና ከክልል ባለድርሻ አካላት እና ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር በመተባበር የፕሮጀክቱን አፈጻጸም ለማሳደግ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

የአሰራር ማዕቀፎችን የማዘጋጀትና የማስተዋወቅ፣ የማስፈጸም አቅም የመገንባት እንዲሁም የክትትል ስራዎች ሲከናወኑ ነበር ማለታቸውን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

በመድረኩ ፕሮጀክቱ ከሚተገበርባቸው የፌዴራል እና የክልል ከተሞች እንዲሁም ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የተወከሉ አመራሮች እና ከፍተኛ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው፡፡

ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ እየተተገበረ የሚገኘው የከተማ ልማት ሴፍቲኔት ስራ እና ፕሮጀክት ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተጋላጭና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ከድህነት እንዲላቀቁ ማስቻሉ በመድረኩ ተነስቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.