Fana: At a Speed of Life!

በማህበራዊ ሚዲያ ለሽብር ወንጀል ቀስቃሽ መልዕክቶችን አስተላልፏል ተብሎ በተጠረጠረው ግለሰብ ላይ የ15 ቀን የክስ መመስረቺያ ጊዜ ተፈቀደ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ፍርድ ቤቱ በማህበራዊ ሚዲያ ለሽብር ወንጀል ቀስቃሽ መልዕክቶችን አስተላልፏል ብሎ ፖሊስ በጠረጠረው ግለሰብ ላይ የ15 ቀን የክስ መመስረቺያ ጊዜ ፈቀደ።

የክስ መመስረቻ ጊዜውን ለዐቃቤ ሕግ የፈቀደው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ነው።

የፌደራል ፖሊስ መርማሪ  አሳዬ ደርቤ በተባለ ተጠርጣሪ ላይ በሽብር ወንጀል መዝገብ ሲያከናውን የቆየውን የማጣሪያ የምርመራ ስራ ማጠናቀቁን እና መዝገቡን ለዐቃቤ ሕግ ማስረከቡን በዛሬው ቀጠሮ ለጊዜ ቀጠሮ ችሎት አስታውቋል።

በመዝገቡ ላይ የተሰየመው የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ከፖሊስ የምርመራ መዝገቡን መረከቡን ገልጿል።

በወ/መ/ስ/ህ/ቁጥር 109/1 መዝገቡን ተመልክቶ ለመወሰንና ክስ ለመመስረት እንዲያስችለው የ15 ቀን ክስ የመመስረቺያ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።

ክስ እስኪመሰርትም ተጠርጣሪው በማረሚያ ቤት ይቆይልኝ በማለት ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱን ዐቃቤ ሕግ ጠይቋል።

የተጠርጣሪ ጠበቃ በበኩላቸው የወ/መ/ስ/ህ / ቁጥር 109/1 የተጠርጣሪውን በስር ለማቆየት ታስቦ የተቀመጠ ድንጋጌ አይደለም በማለት የመከራከሪያ ነጥብ አንስቷል።

ደንበኛቸው በማህበራዊ ሚዲያ አስተላልፏል የተባለው መልዕክት ሕገ መንግስታዊ የሐሳብ ነጻነቱን ተጠቅሞ በመሆኑ እና የተጠረጠረበት የወንጀል ድርጊት ዋስትና መብቱን አያስከለክልም በማለት ተከራክረዋል፡፡

ዐቃቤ ሕግ ሲመራው በቆየበት በሚያውቀው የምርመራ  መዝገብ ላይ እንደ አዲስ ተመልክቼ ክስ ልመስርት ማለቱ ተገቢነት የለውም በማለት ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግ ጥያቄ ውድቅ እንዲያደርግላቸው ጠበቃው ጠይቀዋል፡፡

በተጨማሪም ደንበኛቸው ከዚህ በፊት ክስ ቀርቦበት እንደነበርና በተሰጠው የዋስትና መብት መሰረት በውጭ ሆኖ የሕግ ግዴታውን አክብሮ መቅረቡን በመጥቀስ÷ ቋሚ አድራሻ እንዳለውና የቤተሰብ አስተዳዳሪ ነው በማለት የደንበኛው የዋስትና መብት  እንዲከበር ሲሉ  ጠይቀዋል፡፡

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ተጠርጣሪው የቤተሰብ አስተዳዳሪና ቋሚ አድራሻ ስላለው ብቻ የሽብር ወንጀል ተመልሶ አይፈጽምም ማለት አይቻልም ሲል  ተከራክሯል።

በተጨማሪም ዐቃቤ ሕግ የሐሳብ ነጻነትን በመጠቀም ሕገመንግስቱን በኃይል ለማፍረስ የሽብር ድርጊት እንዲፈጸም፣ የሐይማኖትና የብሔር ግጭት ለማስነሳት ሲያሰናዳ ነበር በማለት በድጋሚ ተመሳሳይ ተግባር ሊፈጽም ይችላል በሚል ስጋቱን ገልጾ የዋስትና ጥያቄውን ተቃውሟል።

የተጠርጣሪ ጠበቃ በበኩላቸው በፍርድ ቤቱ  ጥፋተኛ እስካልተባለ ድረስ ነፃ ሆኖ የመገመት መብቱ ሊጠበቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ወንጀል ሊፈጽም ይችላል ተብሎ የተነሳው ክርክር በቂና አሳማኝ ባለመሆኑ ጥያቄው ውድቅ ይደረግልን ሲሉም ጊዜ ነው ቀጠሮ ችሎቱን ጠይቀዋል።

አጠቃላይ የግራ ቀኙን ክርክር የተመለከቱት ዳኛ  ክስ እስኪመሰረት የተጠርጣሪውን በዋስትና መውጣት እንዳላመኑበት አስረድተዋል፡፡

የተጠርጣሪውን የቆይታ ጊዜ በሚመለከት ግን ባለበት ማረፊያ እንዲቆይ ብይን በመስጠት ዐቃቤ ሕግ የጠየቀውን የ15 ቀን ክስ የመመስረቺያ ጊዜን ፈቅደዋል።

ይሁንና ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ  የሰጠውን የ15 ቀን ክስ የመመስረቻ የትዕዛዝ ውጤት ለመጠባበቅ ለሐምሌ 8 ቀን የቀጠረ ቢሆንም በዕለቱ ችሎቱ ስራ በማይሰራበት ቅዳሜ ዕለት መዋሉን ተከትሎ ወደ አርብ ማለትም ሐምሌ 7 ቀን 2015 ዓ.ም እንዲቀጠር አድርጓል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.