Fana: At a Speed of Life!

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ የእውቅና እና ምስጋና መርሐ ግብር ተካሔደ

 

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ በ2015 ዓ.ም በተመዘገቡ ስኬቶችና የለውጥ ክንውኖች ዙሪያ የእውቅና እና የምስጋና መርሐ ግብር ተካሔደ ፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል እና የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት የወቅቱ ሊቀመንበር ደመላሽ ገብረሚካኤልን ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ጠቅላይ መምሪያው በበጀት ዓመቱ በተከናወኑ የለውጥ ስራዎች ስኬቶችን ማስመዝገብ መቻሉም ተገልጿል።

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል ዘላለም መንግስቴ በዚሁ ወቅት÷ ጠቅላይ መምሪያው በበጀት ዓመቱ በህዝብና ሀገር ላይ የተፈጸሙ ከፍተኛ ወንጀሎችን በመርመር አጥፊዎችን ለህግ ሲያቀርብ ቆይቷል ብለዋል።

ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆንም በተለያዩ አካባቢዎች የታቀዱ ትልልቅ ወንጀሎችን ጉዳት ከማድረሳቸው በፊት ለመቆጣጠር መቻሉንም ተናግረዋል።

በዚሁ ወቅት ሲያካሒድ የቆየው የወንጀል ምርምራ ተግባር የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ያከበሩና የፖሊስ የምርመራ ሰነ-ምግባር መርህን የተከተሉ እንዲሆኑ ለማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል።

በተጨማሪም የሚካሔዱ የምርመራ ስራዎች በተጠርጣሪዎች የወንጀል ድርጊት ላይ ብቻ ያተኮሩ፤ ህግን መሰረት ያደረጉ ናቸው ያሉት ምክትል ኮሚሽነር ጄነራሉ፤ ይሕም የተቋሙን የለውጥ ስራ ውጤታማነት ያመላክታል ብለዋል።

ሙያዊ ብቃትን ያረጋገጠ አካታች እና በህዝብ ታማኝ የሆነ ዘመናዊ የፖሊስ አገልግሎት የመገንባት ራዕይ በመሰነቅም ለተግባራዊነቱ ከፍተኛ ርብርብ በመደረግ ላይ ነው ብለዋል።

ጠቅላይ መምሪያው ባከናወነው የሪፎርም ስራ ዓለም አቀፍ የፖሊስ የምርመራ ደረጃን በማሟላት አገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን በቴክኖሎጂ የታገዙ የምርመራ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ዘመናዊ የቃል መቀበያ ቢሮዎች፣ ተጠርጣሪዎች ከህግ አማካሪዎቻቸው ጋር በነጻነት የሚመካከሩበት ስፍራ፣ የተጠርጣሪ ቤተሰቦች ማረፊያ እና መጠየቂያ ስፍራዎች መገንባታቸውን ለአብነት አንስተዋል።

የተጠርጣሪ ምዝገባና አስተዳደር መረጃዎች ሙሉ በሙሉ በኮምፒውተር የተደራጁ መሆኑንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ÷“ለውጥ የተደረገው የምርመራ ስራውን የሚመሩ አመራሮችና አባላትን በማሰልጠን አመለካከታቸውን በመቀየር ፍፁም ሰብዓዊ መብትና ህግና ስርዓት እንዲያከብሩ ኃላፊነት ወስደው እንዲሰሩ በማድረግ ነው”  ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በሪፎርሙ ከፍተኛ ለውጥ ካመጡ የስራ ክፍሎች አንዱ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ መሆኑን የጠቀሱት ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ያንን አሰቃቂ የሆነ ማዕከላዊ የወንጀል ምርመራ ዘግተን ስራውን ሲሰሩ የነበሩ ኃይሎችን በማሰልጠን አመለካከታቸውን መቀየር እና አንዳንዶቹን በሰሩት ወንጀል ተጠያቂ በማድረግ አሁን ላይ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ በከፍተኛ ደረጃ መቀየሩን በተግባር አሳይቷል ብለዋል፡፡

የወንጀል ምርመራ አቅምን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ በአፍሪካ የልዕቀት ማዕከል ሆኖ የሚሰራ እና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ምርመራዎችን ማድረግ የሚያስችል የፎረንሲክ ላብራቶሪ በውስን አመታት ውስጥ ተጠናቆ ስራ በማስጀመር የትምህርት እና የምርመራ ማዕከል ለማድረግ በኢትዮጵያ ብቸኛ በሆነው የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ እየተገነባ አንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

በማህሌት ተ/ብርሃን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.