Fana: At a Speed of Life!

ከንቲባ አዳነች በ3 ዓመታት ውስጥ የመዲናዋን የአረንጓዴ ሽፋን 30 በመቶ ለማድረስ እየተሠራ ነው አሉ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የአዲስ አበባ ከተማን የአረንጓዴ ሽፋን 30 በመቶ ለማድረስ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የሰላም ሰራዊትን እና የጸጥታ አካላትን በማሳተፍ አንድ ሚሊየን ችግኝ የመትከል መርሐግብር ዛሬ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ተጀምሯል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ÷ ከፌዴራል ፖሊስ አባላት፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት፣ ከደምብ ማስከበር አባላት፣ ከእሳትና ድንገተኛ አደጋ ሰራተኞች፣ ከሰላም ሰራዊት አባላት እና ከሐይማኖት አባቶች ጋር በመሆን 100 ሺህ ችግኞችን ተክለናል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ የአረንጓዴ ሽፋን ከነበረበት 2 ነጥብ 8 በመቶ ባለፉት 4 ዓመታት ወደ 15 በመቶ ማደጉንም ነው ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው የገለጹት፡፡

ዘንድሮም 17 ሚሊየን ችግኞችን በመትከል በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት በአጠቃላይ የሚተከሉትን ችግኞች 50 ሚሊየን ለማድረስ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

በዚህም የከተማችንን የአረንጓዴ ሽፋን ወደ 30 በመቶ በማሳደግ ውብ እና አረንጓዴ፣ ለነዋሪዎች ምቹ አዲስ አበባን የመገንባት ራዕያችንን እውን እናደርጋለን ነው ያሉት።

በዛሬው መርሐግብር 17 ሺህ የሰላም ሰራዊት፣ የፀጥታ አካላትን እና የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.