Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደመቀ መኮንን ከአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ጋር በቢሯቸው ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ትሬንት ኬሊ ጋር ተወያይተዋል።

ሁለቱ ወገኖች የኢትዮ-አሜሪካን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር በሚችሉበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡

በተጨማሪም የምሥራቅ አፍሪካን ወቅታዊ ጉዳዮች አንስተው መወያየታቸው ነው የተነገረው፡፡

የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ትሬንት ኬሊ ÷ የኢትዮጵያ መንግስት የፕሪቶሪያውን የሠላም ሥምምነት አክብሮ ለተፈጻሚነቱ የወሰዳቸውን እርምጃዎችና ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ያደረጋቸውን ማሻሻያዎች አድንቀዋል፡፡

የአሜሪካ መንግስት የሰብአዊ መብት ጥሰት በኢትዮጵያ ተፈፅሟል በሚል የጣለውን ማዕቀብ ለማንሳት መወሰኑም የሀገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት እና ዓለም አቀፍ ትብብር የበለጠ ለማጠናከር ይረዳል ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

ትሬንት ኬሊ አክለውም ÷ ኢትዮጵያ የአሜሪካ ሁነኛ አጋር መሆኗን በመጥቀስ በሌሎች ዘርፎችም ትብብራቸውን ለመቀጠል ቀጣይ ውይይት ማካሄድ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው ÷ በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ስላለው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለአሜሪካ ምክር ቤት ተወካዩ ገልጸውላቸዋል፡፡

ከድኅረ-ጦርነት በኋላ የሚስተዋሉ ጉዳቶች በርካታ እንደመሆናቸው አሜሪካ በሠላም ግንባታ ላይ የሚደረገውን ጥረት መደገፍ እንደሚገባትም አውስተዋል።

አሜሪካ የደረሰችበት ማዕቀብ የማንሳት ውሳኔም አግባብ መሆኑን ጠቅሰው ኢትዮጵያ ድጋፍ ከአሜሪካ ማኅበረሰብ እና ከአሜሪካ መንግስት እንደምትሻ አስረድተዋል፡፡

የመልሶ ግንባታ እና የማቋቋም ሂደቱንም እንዲደግፉ አቶ ደመቀ መኮንን ጠይቀዋል፡፡

ሁለቱ ወገኖች በምሥራቅ አፍሪካ ያለውን የሠላም እና የጸጥታ ችግር ለመፍታት ተቀናጅተው መሥራት እንደሚገባቸው ሥምምነት ላይ ደርሰዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.