Fana: At a Speed of Life!

ለሕዝብ የልማት ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ለመስጠት ገቢን አሟጦ መሰብሰብ ላይ በትኩረት ይሰራል -አቶ አሻድሊ ሃሰን

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለህዝብ የልማት ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ለመስጠት ገቢን አሟጦ መሰብሰብ ላይ በትኩረት እንደሚሠራ የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አሻድሊ ሃሰን ገለጹ።

ለስኬቱ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሠራተኞች የእውቅናና ምስጋና መርሃ-ግብር ዛሬ በአሶሳ ከተማ ሲካሄድ ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት÷ በክልሉ በገቢ አሰባሰብ ሂደት እመርታ እየተመዘገበ ነው።

ይሁንና በክልሉ መልማት ከሚችለው ከፍተኛ የተፈጥሮ ሃብት እንጻር አሁን እየተሰበሰበ ያለው ገቢ ዝቅተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።

በክልሉ በግብርና፣ በማዕድን እና በሌሎች መስኮች የኢንቨስትመንት አቅምን በማጠናከር ገቢን አሟጦ መሰብሰብ የህልውና ጉዳይ ተደርጎ እንደሚሰራም አመልክተዋል።

ከፌዴራል መንግስት የበጀት ድጎማ ለመላቀቅ የራስን አቅም መገንባት ወሳኝ መሆኑን የገለጹት አቶ አሻድሊ÷ ይህም የህዝብን የልማት ጥያቄዎች በአግባቡ ለመመለስና የሃገሪቱን የብልጽግና ጉዞ ለማፋጠን ያግዛል ብለዋል።

የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን አቶ መለሰ ኩዊ በበኩላቸው፣ በክልሉ በ2015 በጀት ዓመት 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን አስታውሰዋል።

ባለፉት 11 ወራት በተሰሩ ሥራዎችም ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ካልሆኑ ታክስ እና ሌሎች የገቢ አርዕስቶች 3 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን ገልጸዋል።

በምግብ ሰብል እና በገቢ አሰባሰብ ራስን መቻል ለአንድ አገር ዋነኛ ጉዳይ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትሩ አቶ ገብረመስቀል ጫላ ናቸው።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን የግብር አሰባሰብ ሂደትን በቴክኖሎጂ የተደገፈ በማድረግ በኩል ከሌሎች ክልሎች መሰል ተቋማት ቀዳሚ መሆኑንም ገልጸዋል።

ለእዚህም የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን ተግባራዊ ያደረገውን የኦንላይን ትሬዲንግ ሲስተም ለአብነት መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የንግዱ ማህበረሰብ ግብሩን በኦንላይን መክፈል ብቻ ሳይሆን ፈቃዱን ከማደስ ጀምሮ ሌሎች አገልግሎቶችን ቴክኖሎጂውን ተጠቅሞ በቀላሉ ማግኘት እንዳለበትም አስገንዘበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.