Fana: At a Speed of Life!

በዓለም ሥርዓት ውስጥ ተወዳዳሪ ለመሆን ትምህርት ቁልፍ መሣሪያ ነው – አቶ ደስታ ሌዳሞ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በዓለም ሥርዓት ውስጥ ተወዳዳሪ ለመሆን ትምህርት ቁልፍ መሣሪያ ነው ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን ያሉት “ጥራት ያለው ትምህርት ለትውልድ” በሚል መሪ ሐሳብ እየተካሄደ ባለው የክልሉ የትምህርት ንቅናቄ መድረክ ላይ ነው።

የክልሉ ም/ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ በራሳ÷በክልሉ ትምህርትን ተደራሽ ለማድረግ ባለፉት ሁለት ዓመታት 83 ትምህርት ቤቶች በመንግስትና በግል ባለሐብቶች መገንባታቸውን አንስተዋል፡፡

ለትምህርት ቤቶቹ ብቁ መምህራንን ለማፍራት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ነው የገለጹት።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፈንታ ማንደፍሮ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷በሀገራችን ካሉት 50 ሺህ ትምህርት ቤቶች መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት ከደረጃ በታች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከደረጃ በታች ማለት ንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ መፀዳጃ ቤቶች ፣ለአካል ጉዳተኞች የሚመች ግንባታ፣ የአይ.ሲ.ቲና ቤተ ሙከራ የሌላቸው ማለት መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተዋል፡፡

የትምህርት ዘርፍ ለተወሰኑ ሰዎችና ተቋማት የማይተው ሁሉም በባለቤት በመስራት ለትውልድ ሊያሸጋግረው የሚገባ ዘርፍም ነው ብለዋል።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ÷ ዛሬ ዓለምን በኢኮኖሚና ፖለቲካ እየመሩ ያሉ ሀገራት መነሻቸው ትምህርት ላይ የሰጡት ትኩረት ነው ብለዋል፡፡

“እኛ ለትምህርት የሰጠነው ትኩረት የዘገየ ቢሆንም አሁን ባገኘነው አጋጣሚ ተጠቅመን ትኩረት በመሥጠት ልጆቻችን እና ሀገርን እንታደግ” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በጥላሁን ይልማና ተመስገን ቡልቡሎ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.