Fana: At a Speed of Life!

የተሠረቁ የመኪና ዕቃዎችን እየገዙ ሲሸጡ የነበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 3 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሱቅ በመከራየት ከተለያየ ቦታ የተሰረቁ የመኪና ዕቃዎችን ከወንጀል ፈፃሚዎች እየገዙ ሲሸጡ የነበሩ 4 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።

ተጠርጣሪዎቹ በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 በተለምዶ ሱማሌ ተራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት።

እንደ ፖሊስ ገለጻ ህብረተሰቡ ለፀጥታ አካላት ባደረሠው መረጃ እና የክፍለ ከተማው ፖሊስ ባደረገው ክትትል በአምስት የመኪና ዕቃ መለዋወጫ መሸጫ ሱቆች ላይ በህግ አግባብ በተከናወነ ብርበራ በርካታ የተሠረቁ የመኪና ዕቃዎች ተገኝተዋል።

135 የፊት መብራት ፣ 143 ፍሬቻ እና 169 ስፖኪዮ ከተያዙት ንብረቶች መካከል የሚገኙ ሲሆን፥ ከዚህ የወንጀል ጉዳይ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር በዋሉት ግለሰቦች ላይ ምርመራ እየተጣራ ይገኛል።

በተለምዶ ሱማሌ ተራ ተብሎ የሚጠራው ይህ አካባቢ ተመሳሳይ ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄድበት መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ፖሊስ እየወሰደ የሚገኘውን ተከታታይነት ያለው እርምጃ አጠናክሮ ይቀጥላልም ብሏል፡፡

ከተለያዩ የመዲናዋ አካባቢዎች የተሰረቁ የመኪና ዕቃዎችን እየገዙ የሚሸጡ የሌባ ተቀባዮች በህግ አግባብ ተጠያቂ እንዲሆኑ ህብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጎን በመሆን እያበረከተ ያለውን አስተዋፅኦ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ፖሊስ ጠይቋል።

በተለያዩ ጊዜያት የመኪና ዕቃ የጠፋባቸው ግለሠቦች ወደ ልደታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ በመምጣት የራሳቸው ንብረት ስለመኖሩ ለይተው በማረጋገጥ መውሠድ የሚችሉ መሆኑንም ፖሊስ መምሪያው ገልጿል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.