Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ እና በሸገር ከተማ የሽብር ጥቃት ለማድረስ ሲንቀሳቀሱ ነበር በተባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከባድ የጦር መሳሪያ በመያዝ በአዲስ አበባ እና ሸገር ከተማ የሽብር ጥቃት ለማድረስ ሲንቀሳቀሱ ነበር በተባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ 10 የምርመራ ቀን ተፈቀደ።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት በመርማሪ ፖሊስ ያቀረበውን የምርመራ ስራ ውጤትና በተጠርጣሪ ጠበቃ የተነሱ መከራከሪያ ነጥቦችን መርምሮ ነው ለፖሊስ የ10 ቀን የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ የፈቀደው።

ተጠርጣሪዎቹ ያድንናኦል ሱራፌል ፣ ሚካኤል ዮሐንስ እና ወላቡ ደረጀ ይባላሉ።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል መርማሪ ተጠርጣሪዎቹ የሸኔ ሽብር ቡድን አባል በመሆን፣ የሽብር ቡድኑ አመራሮች ጋር በአካልና በስልክ በመገናኘት፣ ከሸኔ የሽብር ቡድን አመራሮች ተልኮ በመቀበል፣ ሕገ -መንግስቱንና ሕገመንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ በማቀድ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ጠቅሷል፡፡

ከባድ የብሬን የጦር መሳሪያ እና 2 ሺህ 63 የክላሽ መሳሪያ ጥይቶችን በሀዩንዳይ ተሽከርካሪ በመያዝ በአዲስ አበባ እና ሸገር ከተማ ላይ የሽብር ጥቃት ለማድረስ ሲንቀሳቀሱ በፀጥታ ኃይሎች ክትትል በሰኔ 20 ቀን 2015 ዓ.ም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቁሟል፡፡

ፖሊስ ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ከዚህ በፊት በነበረ ቀጠሮ ማቅረቡ የሚታወስ ሲሆን÷በዛሬው ቀጠሮም ከዚህ በፊት በተሰጠው የ14 ቀን ጊዜ ውስጥ የሰራቸውን የምርመራ ውጤቶችና ቀሪ ሥራዎች ለችሎቱ አቅርቧል።

በዚህም ጊዜ የምስክሮችን ቃል መቀበሉን፣ በመኖሪያ ቤት ብርበራ ማከናወኑን፣ የፎረንሲክና የቴክኒክ የምርመራ ማስረጃዎችን እንዲላኩለት ከሚመለከተው ተቋም መጠየቁን፣ የገንዘብ ዝውውር ለማጣራት ለተለያዩ ባንኮች የማረጋገጫ እንዲሰጠው በደብዳቤ መጠየቁን፣ የተጠርጣሪዎችን ቃል መቀበሉን እና የጣት አሻራና ፎቶ ማስነሳት ስራ ማከናወኑን አብራርቷል።

በተጨማሪም ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ እጅ ተገኝቷል ያላቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ክፍለ ከተሞች ማሕተሞች፣ የተለያዩ ሃሰተኛ ሰነዶች፣ የልደት ካርዶችና ለተለያዩ አባሎቻቸው የሚዘጋጅ የአዲስ አበባ የነዋሪነት መታወቂያዎች ከየት ወጪ እንደተደረጉ የማጣራት ስራ እንደሚቀረው ገልጿል።

እንዲሁም የቀሪ ምስክሮችን ቃል መቀበል፣ የቴክኒክና የፎረንሲክ ማስረጃዎችን ተቀብሎ ከምርመራ መዝገቡ ጋር ለማያያዝ፣ ከባንክና ከጉዳዩ ጋር ተያያዥ ማስረጃዎችን የማስመጣት ስራ እንደሚቀረው ጠቅሶ ተጨማሪ የ14 ቀን ጊዜ ቀጠሮ ጠይቋል።

የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች በበኩላቸው ደንበኞቻቸው ወንጀል አለመፈጸማቸውን ገልጸው ÷ ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ ሊሰጥ እንደማይገባ የመከራከሪያ ነጥብ አንስተዋል።

ፖሊስ ከዚህ በፊት በተሰጠው ጊዜ ውስጥ መጠናቀቅ የነበረባቸው የምርመራ ስራዎችን ሳያጠናቅቅ ቀርቧል በማለት የደንበኞቻቸው የዋስ መብት እንዲከበር ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱን ጠይቀዋል።

በመርማሪ ፖሊስ በኩል የዋስትና ጥያቄያቸውን ተከትሎ የመቃወሚያ የመከራከሪያ ነጥቦች ተነስተዋል።

በዚህም ተጠርጣሪዎቹ በዋስ ቢወጡ ከሽብር ቡድኑ ጋር ሀገርን የማፍረስና የሽብር ተግባር ሊፈጽሙ ይችላሉ ሲል ስጋቱን ጠቅሶ ተከራክሯል።

በተጨማሪም ማስረጃ ሊያሸሹና ምስክርን ሊያስፈራሩብን ይችላሉ በማለት የዋስትና ጥያቄያቸውን ተቃውሟል።

የግራ ቀኙን ክርክር የመረመረው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ተጨማሪ ማጣሪያ ማድረግ እንደሚያስፈልግ በማመን የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ለፖሊስ የ10 ቀን የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.