Fana: At a Speed of Life!

በቀጣይ 10 ቀናት በአንዳንድ አካባቢዎች ስለሚዘንብ ለጎርፍ ተጋላጭ አካባቢዎች እንዲጠነቀቁ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሚቀጥሉት 10 ቀናት በአንዳንድ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ ዝናብ ስለሚኖር ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳሰበ።

በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍሎች መደበኛ ዝናብ እንደሚኖርም ኢንስቲትዩቱ ገልጿል።

የትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ፣ ደቡብ ምዕራብ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝና ሲዳማ ክልሎች መደበኛ ዝናብ ያገኛሉ ብሏል።

ይህም በአካባቢዎቹ ላይ እየተከናወነ ለሚገኘው የግብርና እንቅስቃሴ በጎ ሚና የሚጫወት መሆኑንም አመላክቷል።

የዝናብ ስርጭትና መጠኑ የተሻለ ስለሚሆን የአፈር እርጥበት ለግብርና እንቅስቃሴ ለማከናወን ለተዘሩ ሰብሎች ውሃ ፍላጎት ለማሟላትና የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና የመኖ ሳር ልምላሜ በጎ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ተጠቅሷል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በጅማ፣ ኢሉባቦር፣ አራቱ የወለጋ ዞኖች፣ በሁሉም ሸዋ ዞኖች፣ በምዕራብ ሐረርጌ፣ አርሲና ምዕራብ አርሲ ዞኖች ከመደበኛ በላይ ዝናብ ያገኛሉ ተብሎ ይገመታል።

በአማራ ክልል ምዕራብና ምሰራቅ በጎጃም፣ አዊ፣ ሰሜንና ደቡብ ጎንደር ዞኖች፣ ባህዳር ዙሪያ፣ ዋግ ህምራ፣ ሰሜንና ደቡብ ወሎ እና ሰሜን ሸዋ ዞኖች ከመደበኛ የተቀራረብና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ያገኛሉ።

በዚህም የወንዞች ከገደብ በላይ መሙላት ሊከሰት ስለሚችል ህብረተሰቡና የሚመለከታቸው አካላት በሰው ህይወትም ሆነ በንብረት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ አስፋላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ኢንስቲትዩቱ ማሳሰቡን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.