Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበበ በአንድ ጀንበር ከ3 ሚሊየን በላይ ችግኝ ለመትከል ዝግጅት ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፊታችን ሰኞ ከ3 ሚሊየን በላይ ችግኝ ለመትከል ዝግጅት ማጠናቀቁን አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይም÷ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ሠራተኞች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች፣ የተለያዩ አደረጃጀቶች፣ የስፖርት ቤተሰቦች፣ አርቲስቶች፣ የጸጥታ መዋቅሩን እና የከተማዋን ነዋሪ ያሳተፈ ንቅናቄ ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጀማሉ ጀንበሩ (ዶ/ር) እንዳሉት÷ የችግኝ ተከላው በሁሉም የከተማዋ አካባቢዎች ይከናወናል፡፡
በልዩ ሁኔታም በየወረዳው ለአረንጓዴ ቦታነት ተለይተው በተቀመጡ ቦታዎች፣ በመንገድ አካፋዮች እና ለተከላ ምቹ ይሆናሉ ተብለው በተለዩ አካባቢዎች ላይ ችግኝ ተከላው እንደሚከናወን አንስተዋል፡፡
በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ላይ÷ ለከተማ ጥላ ዛፍነት እና ለውበት የሚሆኑ እንዲሁም የፍራፍሬ ችግኞች እየተተከሉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
በአጠቃላይ እንደ ከተማ አስተዳደር በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር 17 ሚሊየን ችግኞች እንደሚተከሉ ጠቁመዋል፡፡
‹‹ነገን ዛሬ እንትከል›› በሚል መሪ ሐሳብ እየተከናወነ የሚገኘው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር እንደ ከተማ አስተዳደር ከሰኔ 11 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ እየተከናወነ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
እስካሁንም 8 ነጥብ 4 ሚሊየን ችግኞች መተከላቸውን ነው ጀማሉ ጀንበሩ (ዶ/ር) ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያረጋገጡት፡፡
የችግኝ ተከላው እስከ ሐምሌ መጨረሻ ድረስም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው÷ እስካሁን ባለው እንቅስቃሴም ከ900 ሺህ በላይ የከተማዋ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል ነው ያሉት፡፡
የፊታችን ሰኞ በሚከናወነው በአንድ ጀንበር ከ3 ሚሊየን በላይ ችግኝ የመትከል መርሐ ግብር ላይ መላው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ ቀርቧል፡፡
በዮሐንስ ደርበው
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.