Fana: At a Speed of Life!

ከንቲባ አዳነች በአዲስ አበባ የትምህርት ቤቶች መሰረተ ልማት ንቅናቄን አስጀመሩ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2015(ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዲስ አበባ የትምህርት ቤቶች መሰረተ ልማት ንቅናቄን ዛሬ አስጀምረዋል።

በንቅናቄው ማስጀመሪያ ላይ የፌደራል መንግስት እና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ተገኝተዋል።

ንቅናቄው የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ያለመ ነው።

ከንቲባ አዳነች በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ “ትውልድ ላይ ኢንቨስት ማድረግ ለሀገር ግንባታ መሰረት ነው” ብለዋል።

ትምህርት ቤቶች እየገጠማቸው ያሉ ችግሮችን ለመፍታት በቅንጅት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በዚህም የሚያስፈልጓቸውን የትምህርት መሰረተ ልማቶች በማሟላት የመማር ማስተማሩን ስራ ምቹ ማድረግ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

በከተማ ደረጃ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ትምህርት ቤቶች ደረጃቸውን ያላሟሉ መሆናቸውን ጠቁመው÷  ችግሮቹን ለመፍታት ርብርብ እንደሚያስፈልግ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ በመዲናዋ በርካታ ትምህርት ቤቶች አሁንም በሚጠበቀው ደረጃ ላይ አለመድረሳቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ደረጃቸውን ለማሻሻልም የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የትምህርት ቤቶችን መሰረተ ልማት ማሟላት፣ የመምህራንን አቅም እና ተነሳሽነት ማጎልበት የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል ከተጀመሩ እንቅስቃሴዎች መካከል መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.