Fana: At a Speed of Life!

ዐቃቤ ህግ አሳዬ ደርቤ በተባለ ግለሰብ ላይ ሀሰተኛና የጥላቻ ንግግር ማሰራጨት የወንጀል ክስ መሰረተ

 

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 7 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዐቃቤ ህግ አሳዬ ደርቤ በተባለ ግለሰብ ላይ ሀሰተኛና የጥላቻ ንግግር ማሰራጨት የወንጀል ክስ መሰረተ።

የፍትህ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዐቃቤ ህግ በግለሰቡ ላይ ተደራራቢ ሰባት ክሶችን ነው ያቀረበው።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረ ሽብርና የህገመንግስት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በዐቃቤ ህግ የተመሰረተው የክስ ዝርዝር ከሰነድና ከአንድ የሲዲ ማስረጃ ጋር ለተከሳሹ እንዲደርስ አድርጓል።

ለተከሳሹ እንዲደርስ በተደረገው በአንደኛ ክስ ላይ እንደተመላከተው የወንጀል ህግ አንቀጽ 257/ሀ በመተላለፍ ተከሳሹ በፌደራል ህገ መንግስት ስልጣን የተሰጠውን የኢፌዴሪ የሃገር መከላከያ ሰራዊት ስራውን ወይም ተግባሩን እንዳያከናውን ለማደናቀፍ በማሰብ በግንቦት 28 ቀን 2015 ዓ.ም ተከሳሹ በሚጠቀመው የስልክ ቁጥር እና በራሱ ስም በከፈተው የቴሌግራም ገጽ ላይ ገዳም ውስጥ ያሉ መነኮሳትን የፌጢኝ አስሮ የሚረሽነው የአብይ ሰራዊት ከአማራ ክልል ተጠራርጎ መውጣት ይገባዋል በማለት የመገፋፋት ተግባር ፈጽሟል በሚል ነው ክስ ያቀረበበት።

በሁለተኛው ክስ ደግሞ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 255 ንዑስ ቁጥር 1 እንዲሁም የኮምፒዩተር ወንጀልን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር  958/2008 አንቀጽ 18 በመተላለፍ ተከሳሹ በህገመንግስት በተቋቋሙ አካላት ላይ ህዝብ የትጥቅ ትግል እንዲያነሱ በማሰብ በስሙ በተከፈተ በዩቲዩብ ገጹ ላይ በሚያዚያ 22 ቀን 2015 ዓ.ም  ”ወቅታዊ ጉዳይ” በሚል ርዕስ ባሰራጨው ቪዲዮ ላይ ”መንግስት ከህወሓት ጋር በፕሪቶሪያ ስምምነት ያደረገው በሀገሪቱ ሰላም ለማምጣት አይደለም ውይይቱ የተደረገው አንድ ላይ ሆነን አማራን እናጥቃ በሚል ነው ” በማለት በኮምፒዩተር አማካኝነት መንግስት ላይ ወንጀል እንዲፈጸም የማነሳሳት ተግባር የሚል ክስ ዐቃቤ ህግ አቅርቦበታል።

በሌላኛው በሶስተኛ ክስ ላይ ደግሞ የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1185/2012 አንቀጽ 5 እና/ ንዑስ ቁጥር 4ን በመተላለፍ ግለሰቡ በግንቦት 19 ቀን 2015 ዓ.ም በዩቲዩብ ገጹ ላይ ”ወቅታዊ ጉዳይ ”በሚል ርዕስ ባሰራጨው ቪዲዮ ላይ ”በብልፅግና ስርዓት የሙስሊሞችን ያህል ተጠቂ የለም ” በተለይም የአማራ ሙስሊሞች ገዢው ፓርቲ የአማራ የትግል አመራሮችን ለመግደል በደህንነት ኃይል ስምሪት ተሰማርቷል” በማለት እንዲሁም ” ብአዴን ህዝቡን ትጥቅ አስፈትቶ ለኦሮሙማ ሊያስረክብ ነው ”በማለት ሃሰተኛ መረጃ አሰራጭቷል የሚል ክስም በዐቃቤ ህግ ቀርቦበታል።

በአራተኛ ክስ በሚመለከት ደግሞ ተከሳሹ በየካቲት 17 ቀን 2015 ዓ.ም በዩቲዩብ ገጹ ላይ ”ከትጥቅ ማስፈታት ወደ ትጥቅ መስጠት የተሸጋገረ ስምምነት ” በሚል ባሰራጨው ተንቀሳቃሽ ቪዲዮ ላይ ”ገዢው መንግስት በሸገር ከተማ ምንም አይነት አማርኛ ተናጋሪ ነዋሪ እንዳይኖር ማፈናቀልና ማባረር ይኖርብናል የሚል አጀንዳ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ነው ” በማለት ሃሰተኛ መረጃን ያሰራጨ መሆኑን ጠቅሶ ዐቃቤ ህግ በክሱ ላይ አስፍሯል።

በዚህ መልኩ የቀረበበትን ሰባት ተደራራቢ ክሶች ተመልክተው የዋስትና ክርክር ለማድረግ እንዲችሉ ፍርድ ቤቱ አጭር ቀጠሮ እንዲሰጣቸው የተከሳሽ ጠበቃ ጠይቀዋል።

ፍርድ ቤቱም ለፊታችን ሰኞ ሐምሌ 10 ቀን ረፋድ 4:00 ላይ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.