Fana: At a Speed of Life!

ዘንድሮ ከሚተከለው ችግኝ 60 በመቶው ፍራፍሬ ነው

አዲስ አበባ፣  ሐምሌ 8፣ 2015 (ኤፍ ቢሲ) በሀገር አቀፍ ደረጃ ዘንድሮ ከሚተከለው 6 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኝ 60 በመቶው ፍራፍሬ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

 

ዘንድሮ ከሚተከለው ችግኝ 60 በመቶው ፍራፍሬ፣ 35 በመቶው የደን እና 5 በመቶው ለከተማ ውበት የሚሆኑ ናቸው ተብሏል።

 

የፊታችን ሰኞ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከጠዋቱ 12 ሠዓት እስከ አመሻሽ 12 ሠዓት በአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር እንደሚከናወን የሚኒስቴሩ የተፈጥሮ ሐብት ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ አንተነህ ፈቃዱ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

 

ለዚህ የአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ መርሐ ግብርም 9 ሺህ 500 ቦታዎች ካርታ (ጂኦስፓሻል ማፕ) ተዘጋጅቷል ብለዋል።

 

በዕለቱ የሚተከሉት ችግኞች ቆጠራ እንደተፈጸመም መረጃው ወደ ካርታው ሥርዓት ውስጥ እንደሚገባ አመላክተዋል።

 

ይህንንም በ https://www.greenlegacy.et/green-legacy/home ድረ ገጽ መከታተል እንደሚቻል ነው የጠቆሙት።

 

ኢትዮጵያ በሁለተኛው ምዕራፍ (ከ2015 እስከ 2018 ዓ.ም) የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር 25 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል አቅዳ እየሠራች መሆኑ ተመልክቷል።

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሁለተኛውን ምዕራፍ የመጀመሪያ ዓመት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር ሰኔ 1ቀን 2015 ዓ.ም በአፋር ክልል ማስጀመራቸው ይታወሳል።

 

በአጠቃላይ የዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር እንደየአካባቢው  ሥነ-ምኅዳራዊ ሁኔታ ቢወሰንም እስከ መስከረም 2016 ዓ.ም ድረስ እንደሚዘልቅ ተጠቅሷል።

 

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.