Fana: At a Speed of Life!

ዓላማችን ሪከርዳችንን መስበር ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓላማችን ሪከርዳችንን መስበር ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሳፈሩት ጽሑፍ ÷ የአረንጓዴ ዐሻራ ጉዳይ ኢትዮጵያን የመጠበቅ፣ የማክበርና የማበልጸግ እንዲሁም ታሪክ የመቀየርና ለትውልድ የመትረፍ ጉዳይ ነው ብለዋል።

ከማኅበራዊ እና ሃይማኖታዊ ተግባራት ነጻ የሆነ ቀን የመረጥነው ይህ ቀን ሊያልፈው የሚገባ ኢትዮጵያዊ ሊኖር ስለማይገባ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ሰኞን ስንመርጥ የሥራ መጀመሪያችንን ተፈጥሮን በመታደግ እንድንጀምር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ፉክክራችንም ከራሳችን ጋር ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ክልሎች፣ ዞኖች፣ ወረዳዎች እና መንደሮች ከአምናው የበለጠ በመትከል የየራሳቸውን ሪከርድ እንደሚሰብሩ እናምናለንም ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር ) እያንዳንዱ ዜጋ በነገው ዕለት የራሱን ሪከርድ መስበር እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

ችግር የራሱን ሪከርድ እንዲሰብር ልንፈቅድለት አይገባም፤ችግር የራሱን ሪከርድ ከሰበረ ተሸንፈናል ማለት ነው ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡

“ችግር የራሱን ሪከርድ ከሰበረ ተሸንፈናል ማለት ነው፤ ችግርን የምናሸንፈው መጀመሪያ የራሳችንን ፣ ቀጥሎ የአካባቢያችንን ፣ በመጨረሻም የዓለምን ሪከርድ ስንሰብር ነው።” በማለት ለመልዕክታቸው አፅንዖት ሰጥተዋል፡፡

ዜጎች ነገ ሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም የራሳቸውን ሪከርድ በብዙ መጠን እስኪሰባብሩ ድረስ ዛፎችን ለመትከል እንዲዘጋጁ ጠቁመዋል፡፡

እኔ ነገ በተደጋጋሚ ለመትከል ተዘጋጅቻለሁ። እናንተስ? ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.