Fana: At a Speed of Life!

ለዓለም አየር መበከል ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዙት አሜሪካና ቻይና በጉዳዩ ላይ ሊመክሩ ነው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለማችን የአየር ንብረት ለውጥ ላይ ተፅዕኖ በማሳረፍ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዙት አሜሪካ እና ቻይና በጉዳዩ ላይ አፅንዖት ሰጥተው ሊመክሩ መሆኑ ተገለጸ፡፡

በዓየር ንብረት ላይ የአሜሪካ መልዕክተኛ ጆን ኬሪ ከአቻው ዢ ዤንዋ ጋር ለመምከር በዛሬው ዕለት ወደ ቻይና ማቅናታቸውን ኤ ኤፍ ፒ ዘግቧል፡፡

ሁለቱ ታላላቅ፣ በኢንዱስትሪ የበለጸጉ እና ለአየር ብክለት ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዙት አሜሪካ እና ቻይና ከዚህ ቀደም በዓለም ሙቀት መጨመር ጉዳይ ጀምረው ያቋረጡትን ውይይት እንደገና አፅንዖት ሰጥተው ይጀምራሉ ተብሏል።

ባለፈው ዓመት አሜሪካ እና ቻይና በዓየር ንብረት ለውጥ ላይ ለመደራደር ተቀምጠው እንደነበር ይታወሳል፡፡

ነገር ግን የወቅቱ የአሜሪካ ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ናንሲ ፔሎሲ ታይዋንን መጎብኘታቸውን ተከትሎ ቻይና በመቆጣቷ በሀገራቱ መካከል ሲካሄድ የነበረው የአየር ንብረት ለውጥ ድርድር ዕልባት ሳያገኝ ቆይቷል፡፡

ጆን ኬሪ ከቻይና ባለሥልጣናት ጋር በሚኖራቸው ቆይታ የፊታችን ኅዳር 30 በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የሚካሄደውን 28ኛው የዓየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ የተሳካ ለማድረግ ይወያያሉ ተብሏል፡፡

በፈረንጆቹ የፊታችን ኅዳር 2023 የዓለም ሙቀት መጨመር እና ተጽዕኖዎቹን መቅረፍ ላይ ያተኮረ የተመድ 28ኛው ጉባዔ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ይካሄዳል፡፡

በጉባዔው ወደ 200 የሚጠጉ የዓለማችን ሀገራት ተቀምጠው ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.