Fana: At a Speed of Life!

የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ለ2016 በጀት ዓመት ከ22 ቢሊየን 637 ሚሊየን ብር በላይ በጀት አጸደቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሲዳማ ክልል ምክር ቤት እያካሄደ ባለው መደበኛ ጉባኤ ለ2016 በጀት ዓመት የቀረበለትን ከ22 ቢሊየን 637 ሚሊየን ብር በላይ በጀት አጸደቀ።

በበጀት ዓመቱ በክልሉ የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የነዋሪውን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራም ተገልጿል።

የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ ዶክተር አራርሶ ገረመው የበጀት ረቂቁን እና በጀቱ የሚውልባቸውን የልማት መስኮች በዝርዝር ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።

በጀቱ በክልሉ ለሚካሄዱ የዘላቂ ልማት ግቦችና ለአስተዳደራዊ ተግባራት እንደሚውል ባቀረቡት የበጀት ረቂቅ አመልክተዋል።

በጀቱ ለክልል ማዕከል፣ ሀዋሳን ጨምሮ ለዞን፣ ለከተማና ለወረዳ አስተዳደሮች እንደሚውልም ነው የተገለጸው።

በቀረበው የበጀት ረቂቅ ላይ የምክር ቤቱ አባላት የተለያዩ አስተያየቶችን አንስተዋል።

በእዚህም በበጀቱ ለድህነት ቅነሳ፣ ለመሠረተ ልማት ዝርጋታ እንዲሁም የነዋሪውን የልማት ተጠቃሚነት ለሚያረጋግጡ ተግባራት ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ የ2016 በጀት ዓመት የክልሉን መንግስት የትኩረት አቅጣጫ ዛሬ ለምክር ቤቱ ያቀረቡ ሲሆን÷ የምክር ቤቱ አባላትም በቀረበው የሥራ ዕቅድ የትኩረት አቅጣጫ ላይ ተወያይተው አፅድቀዋል።

የምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባም በነገው እለት የሚቀጥል ሲሆን÷ የተለያዩ አዋጆችንና ሹመቶችን በመስጠት ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.