Fana: At a Speed of Life!

ማእከሉ ድጋፍ የሚያደርግላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ቁጥር ከ3 ሺህ በላይ ለማድረስ ወደ ስራ መግባቱን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል የሚገኘው ፍሬምናጦስ የአረጋውያን፣ የአእምሮ ህሙማንና የህፃናት መርጃ ማእከል ድጋፍ የሚያደርግላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ቁጥር ከ3 ሺህ በላይ ለማድረስ የሚያስችለውን ቦታ ተረክቦ ወደ ስራ መግባቱን አስታወቀ።

የማእከሉ መስራችና ስራ አስኪያጅ አባ ገብረመድህን በርሄ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ማእከሉ በቀጣይ አምስት አመታት ውስጥ ድጋፍ የሚያደርግላቸውን ወገኖች ቁጥር ለማሳደግና አገልግሎቱን ለማስፋት የሚያስችሉ ተግባራት እያከናወነ ነው።

ማእከሉ አሁን ላይ ከመቀሌ ከተማ አስተዳደር በተረከበው 43ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ባለሶስት ፎቅ አገልግሎት መስጫ ህንጻ ግንባታ ለማካሄድ ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።

የህንጻ ግንባታው ከ400 በላይ አገልግሎት መስጫ ክፍሎች የሚኖሩት ሲሆን ከ2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ እንደሚደረግበት ጠቁመዋል።

የህንጻ ግንባታው ህክምና መስጫና ማገገሚያ ማእከል፣ የሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ፣ የመዝናኛ ማእከል፣ መሰብሰቢያ አዳራሽና ሌሎች አገልግሎት መስጫዎችን እንደሚያካትት ጠቅሰዋል።

የህንጻው ግንባታ በመጭዎቹ አራት አመታት ሲጠናቀቅ ማእከሉ አሁን ላይ ድጋፍ የሚያደርግላቸው 300 የህብረተሰብ ክፍሎች ቁጥር ከ3 ሺህ በላይ ለማሳደግ እንደሚያስችለው መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ከአምስት አመት በፊት በተከራየው ህንጻ 26 ህሙማንን በመቀበል ስራውን የጀመረው ማእከሉ አሁን ላይ በመቀሌና በዓዲግራት ከተሞች ለ150 የአእምሮ ህሙማን፣ ለ50 ወላጅ አልባ ህጻናትና ለ100 ጠዋሪ ያጡ አረጋውያን ድጋፍ እየሰጠ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.