Fana: At a Speed of Life!

በአፋር ክልል ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ 21 ወረዳዎች ተለይተዋል

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፋር ክልል ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ 21 ወረዳዎች ተለይተው በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ከ21 ወረዳዎች መካከል በአዋሽ ወንዝ አቅራቢያ የሚገኙ 13 ወረዳዎች ከፍተኛ ተጋላጭ መሆናቸውን በኮሚሽኑ የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዳይሬክተር ማሄ አሊ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል፡፡

እንደ ክልል ከ136 ሺህ በላይ ነዋሪዎች በያዝነው የክረምት ወቅት የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነት ስጋት እንዳለባቸውም ነው የጠቆሙት፡፡

ከእነዚህ መካከል ከ49 ሺህ በላይ የሆኑ ነዋሪዎች በአዋሽ ወንዝ አቅራቢያ የሚገኙ በመሆናቸው ከፍተኛ ተጋላጭ ስለሆኑ ለጊዜው ወደ ሌላ አካባቢ እንዲሰፍሩ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ለዚህም ከክልል እስከ ወረዳ ያለውን የመንግሥት መዋቅር እንዲሁም አጋር አካላትን ያካተተ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሠራ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎችን ኮሚሽኑ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ለሕዝቡ እያደረሰ እና የግንዛቤ ማስጨበጥ ተግባራት እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የአደጋ ተጋላጭነቱ በክልሉ በሚጥለው ዝናብ ብቻ አለመገደቡን ጠቅሰው÷ ከአጎራባች ክልሎች ወደ አዋሽ ወንዝ የሚቀላቀሉ ገባር ወንዞችን ታሳቢ ያደረገ ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡

ሕብረተሰቡ ከስጋት ቀጣናው እንዲወጣ እንዲሁም ዝግጁ እንዲሆን እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው÷ እንደ ክልል የጎርፍ አደጋ መጠባበቂያ ዕቅድ መዘጋጀቱን አረጋግጠዋል፡፡

በአለፈው ዓመት በተሠሩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች የከፋ ጉዳት አለመድረሱን አመላክተዋል፡፡

በ2012 ዓ.ም በክልሉ በደረሰ ከፍተኛ የጎርፍ አደጋከ 240 ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን እና ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ዋጋ ያለው ንብረት መውደሙን አስታውሰዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.