Fana: At a Speed of Life!

ፍርድ ቤቱ ዶላር አሽሽተዋል ተብለው በሙስና ወንጀል በተከሰሱ ተከሳሾች ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ ሰጠ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ዶላር አሽሽተዋል ተብለው በሙስና ወንጀል በተከሰሱ ተከሳሾች ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ ሰጠ፡፡

ፍርድ ቤቱ በተከሳሾቹ ላይ የቀረበ የዓቃቤ ህግ የሰው ምስክርና የሰነድ ማስረጃን መርምሮ ነው ፍርድ የሰጠው።

ተከሳሾቹ 1ኛ በጉምሩክ ኮሚሽን የቦሌ ኤርፖርት ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሰራተኛ የሆነው አዲስ አለም ድረስ እና 2ኛ ነጋዴ ነው የተባለው ህይወት መልኩ ታደሰ ናቸው።

በተከሳሾቹ ላይ የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ አቅርቦት የነበረው ክስ ላይ 1ኛ ተከሳሽ የአዲስ አበባ ኤርፖርት ጉምሩክ ቅ/ጽ/ቤት የሰነድ ምርመራ ባለሙያ ሆኖ በሚሰራበት ጊዜ የማይገባ ጥቅም ለራሱ እና ለ2ኛ ተከሳሽ ለማስገኘት በማሰብ በመመሳጠር ያለአግባብ ዲክላራሲዮን እንዲሰራ የጉዞ መረጃ ሰነድ ሰጥቷል ሲል ተመላክቷል።

የብሔራዊ ባንክን የብር እና የውጭ ምንዛሬ አያያዝ ወሰን መመሪያ በመተላለፍ 2ኛ ተከሳሽ በእለቱ የውጭ ጉዞ ታሪክ የሌለው እና ምንም አይነት የውጭ ምንዛሬ ወደ ሀገር ውስጥ ይዞ ባልገባበት ሁኔታ በተጭበረበረ መንገድ ይዞ እንደገባ በማስመሰል መመዝገቡን ዐቃቤ ህግ በክሱ ጠቅሷል።

በዚህ መልኩ ነጋዴ ነው የተባለው 1ኛ ተከሳሽ በሚያዚያ 15 ቀን 2010 ዓ.ም ከውጭ ሀገር በቦሌ አየር ማረፊያ በኩል የውጭ ምንዛሬ ይዞ ባልገባበት ሁኔታ 350 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ከውጭ ሀገር ይዞ እንደመጣ በማስመሰል ዲክሌር አስደርጓል ሲል ዐቃቤ ህግ በክሱ ዘርዝሯል።

በዚህ መልኩ 2ኛ ተከሳሽ በህገወጥ መንገድ ዲክሌር ካስደረገ በኋላ በንግድ ባንክ በከፈተው የዲያስፖራ ሂሳብ ገንዘቡን ገቢ በማድረግ ከ350 ሺህ ዶላር ውስጥ 166 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ወደ ውጭ ባንክ ያስተላለፈ እና የተጠቀመበት መሆኑን ዐቃቤ ህግ በክሱ ጠቅሷል።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ተከሳሾቹ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀፅ 32 ንዑስ ቁጥር 1 /ሀ እና አንቀፅ 33 እንዲሁም የሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 9 ንዑስ ቁጥር 1 /ሀ እና 2 ላይ የተደነገገውን ተላልፈዋል ሲል 1ኛ ተከሳሽ በዋና ወንጀል አድራጊነት 2ኛ ተከሳሽ ደግሞ በልዩ ወንጀል ተካፋይነት ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።

ከተከሳሾች መካከል 2ኛ ተከሳሽ ብቻ ችሎት ቀርቦ ክሱ የደረሰው እና ጉዳዩን የተከታተለ ሲሆን 1ኛ ተከሳሽ ግን በተደጋጋሚ በተደረገ ጥሪ ባለመቅረቡ ምክንያት በሌለበት ነው ጉዳዩ የታየው።

ይሁንና 2ኛ ተከሳሽ ክሱ ከደረሳቸውና በንባብ ከተሰማ በኋላ ወንጀሉን አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው የዕምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠታቸውን ተከትሎ ዐቃቢህግ ሰባት የሰው ምስክሮችን አቅርቦ አሰምቶ ነበር።

ፍርድ ቤቱም የተሰሙ የምስክሮችን ቃል መርምሮ አንደኛ ተከሳሽ ወንጀሉ መፈጸሙን በምስክር መረጋገጡን በመግለፍ የጥፋተኝነት ፍርድ በሌለበት አስተላልፎበታል።

ሁለተኛ ተከራሽን በሚመለከት በተከሰሱበት አንቀጽ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል።

የሁለተኛ ተከሳሽ የመከላከያ ማስረጃ ካለ ለመጠባበቅ ለሀምሌ 19 ቀን 2015 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.