Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ሳኅለወርቅ ዘውዴ የጤና ዐውደ-ርዕይን ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳኅለወርቅ ዘውዴ በሣይንስ ሙዚየም የተከፈተውን ሀገር አቀፍ የጤና አውደ ርዕይ ጎብኝተዋል፡፡

በጉብኝታቸው ወቅትም÷ ጤና የሁሉም ነገር መሰረት መሆኑን እና ጤናው የተጠበቀ ሕዝብ ከሌለ ጤናማ ሀገር ሊኖር እንደማይችል አስረድተዋል፡፡

ጤና መሰረታዊ የሰው ልጆች መብት ስለሆነ መንግስት ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ መሆኑን እማኝ የሆነ ዐውደ-ርዕይ ነው ብለዋል፡፡

ዐውደ-ርዕዩ ብዙ ትምህርት እየተሰጠበት እንደሚገኝ እና ህክምናን በጥራት ለሁሉም ዜጎቻችን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን መመልከት ችያለሁ ማለታቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

የጤና አገልግሎትን ማቅረብ የመንግስት ብቻ ሳይሆን የግል ዘርፉና የማህበረሰቡ ተሳትፎም አስፈላጊ መሆኑን ማየት መቻላቸውንም ተናግረዋል፡፡

ከውጭ የሚገቡ መድሃኒቶችን በሀገር ውስጥ የማምረት ሂደት አበረታች መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

ዐውደ-ርዕዩን ወጣቶች መጥተው ቢጎበኙ የስራ ፈጠራ ተነሳሽታቸውን እና አእምሮን በማበልጸግ በኩል ፋይዳ ሊኖረው እንደሚችል አስገንዝበዋል፡፡

ዐውደ-ርዕዩ በጤናው ዘርፍ ጥራትን፣ ፈጠራን እና ቴክኖሎጂን አካቶ ማቅረብ የቻለ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡

አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በገጠር ለሚኖሩ ማህበረሰቦች ተደራሽ ለማድረግ መስራት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.