Fana: At a Speed of Life!

የሐረሪ ክልል የ2016 በጀት ከ4 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ እንዲሆን ወሰነ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 13 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረሪ ክልል መስተዳድር ካቢኔ የ2016 በጀት ዓመት ከ4 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ እንዲሆን ውሳኔ አሳልፏል።

ካቢኔው ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ በክልሉ የ2015 በጀት ዓመት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት እና የ2016 በጀት እቅድ ላይ ተወያይቷል።

በዚህም ለክልሉ 2016 በጀት ዓመት በክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ተዘጋጅቶ የቀረበውን ከ4 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ረቂቅ በጀትን ተቀብሎ ለክልሉ ምክር ቤት እንዲጸድቅ ውሳኔ አሳልፏል።

በጀቱ 2 ነጥብ 243 ቢሊየን ብር ከክልሉ ገቢ የሚሰበሰብ ሲሆን ቀሪው ከፌደራል መንግስት ድጎማና ከሌሎች የሚገኝ መሆኑን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።

ከተያዘው በጀት ውስጥ 55 በመቶው የካፒታል በጀት ሲሆን 45 በመቶው ደግሞ ለመደበኛ ወጪዎች የሚውል መሆንኑ በበጀት እቅዱ ላይ ተመላክቷል።

በጀቱ ከአምናው ጋር ሲነጻጸር በ25 በመቶ ብልጫ እንዳለው በበጀት እቅዱ ተጠቅሷል።

የክልሉ ርዕሰ መስተደድር አቶ ኦርዲን በድሪ በጀቱ በክልሉ የተቀመጡ ግቦችን ውጤታማ ለማድረግ የመንግስት ሃብት ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶ መስራት ይገባል ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.