Fana: At a Speed of Life!

ከ71 ቢሊየን ብር በላይ በኤሌክትሮኒክ የክፍያ ሥርዓት የነዳጅ ግብይት ተፈጸመ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ71 ቢሊየን ብር በላይ በኤሌክትሮኒክ የክፍያ ሥርዓት የነዳጅ ግብይት መፈጸሙን የኢትዮጵያ ነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

የኤሌክትሮኒክ ክፍያ ሥርዓት ግብይቱ የነዳጅ ስርቆትን እና ብክነትን በመቀነስ አቅርቦት ከፍ እንዲል ማድረጉን በባለስልጣኑ የነዳጅ ውጤቶች ግብይት ስታንዳርድ ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር ለሜሳ ቱሉ ተናግረዋል፡፡

ቴክኖሎጂውን በማቅረብ እና በመጠቀም ረገድ እንዲሁም ከቴክኖሎጂው ውጭ በጥሬ ገንዘብ ግብይት መፈጸሙ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ያጋጠሙ ችግሮች መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

ሕጋዊ አሠራሩን ጥሰው ሽያጭ ሲፈጽሙ በተገኙ በርካታ ማደያዎች ላይ እርምጃ መወሰዱንም አቶ ለሜሳ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

በያዝነው በጀት ዓመትም የነዳጅ ማጓጓዝን እና ሽያጭን ሙሉ በሙሉ በቴክኖሎጂ የተደገፈ በማድረግ የክትትልና ቁጥጥር ተግባራት እንዲጠናከሩ አቅጣጫ መቀመጡን አመላክተዋል፡፡

የኔትወርክ አቅርቦት ከሌለባቸው አንዳንድ አካባቢዎች በስተቀር የኤሌክትሮኒክ ነዳጅ ግብይቱ በመላ ኢትዮጵያ እየተተገበረ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡

ነዳጅን በኤሌክትሮኒክ ግብይት አልፈጽምም የሚሉ ነዳጅ ማደያዎች ሲያጋጥሙ ተገልጋዮች ትክክለኛ ማስረጃ ለባለስልጣኑ ቢያደርሱ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም ጠቁመዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.