Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ አበባ – ጂቡቲ ኮሪደር በ730 ሚሊየን ዶላር የግንባታ ማሻሻያ ሊደረግለት ነው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ -ጂቡቲ ኮሪደር የግንባታ ማሻሻያ ሊደረግበት መሆኑን የዓለም ባንክ አስታውቋል፡፡

ባንኩ ትናንት ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው÷ የአዲስ አበባ ጅቡቲ ኮሪደር አዲስ በጸደቀው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ቀጠናዊ የኢኮኖሚ ኮሪደር ፕሮጀክት መሰረት የማሻሻያ ግንባታ ይደረግለታል፡፡

ይህም ወደብ አልባ የሆነችውን ኢትዮጵያ ከጅቡቲ ወደብ ጋር በቀላሉ ለማገናኘት እና በምስራቅ አፍሪካ ያለውን የንግድ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ነው የተባለው፡፡

ለማሻሻያ ፕሮጀክቱ የሚውለው 730 ሚሊየን ዶላር ከዓለም አቀፉ ልማት ማህበር (አይ ዲ ኤ) መገኘቱንም ባንኩ አስታውቋል።

የአዲስ አበባ-ጅቡቲ ኮሪደር ወሳኝ የንግድ መስመር ሲሆን 95 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ የወጪ እና ገቢ ንግድ የሚካሄድበት የንግድ መስመር ነው፡፡

የማሻሻያ ፕሮጀክቱም ከድሬዳዋ መኤሶ ድረስ ያለውን ጨምሮ ወደ ጅቡቲ የሚወስደውን መንገድ ደረጃ ለማሳደግ ያለመ መሆኑም ነው የተገለጸው።

የዚህ መንገድ ደረጃ መሻሻል ወደ ጅቡቲ የሚጓዙ አሽከርካሪዎች በሚሌ በኩል አድርገው ተጨማሪ ኪሎ ሜትሮችን እንዲጓዙና ለአላስፈላጊ እንግልት እንዳይዳረጉና በንብረት ላይ የሚደርሰውን ኪሳራ ያስቀራልም ነው የተባለው።

የድሬዳዋ መኤሶ መንገድም በባለ አራት መስመር የፍጥነት መንገድ ደረጃ ማሻሻያ እንደሚደረግለት ባንኩ አመላክቷል።

የአዲስ ጅቡቲ ኮሪደር የግንባታ ማሻሻያ ፕሮጀክት ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማትን በማስተዋወቅ፣ ድህነትን በመቀነስ አፍሪካ በዓለም ኢኮኖሚ ያላትን ተወዳዳሪነት እንደሚያሳድግ ተገልጿል።

እንደ ባንኩ መረጃ ፕሮጀክቱ የሎጂስቲክስ አቅርቦትን በማሻሻል የኢትዮጵያን የንግድ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ይረዳል ተብሎም ይታመናል።

በተጨማሪም ፕሮጀክቱ በሚተገበርባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከዋናው መንገድ ጋር በማገናኘት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እንደመሚያሳድግም ታምኖበታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.