Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደመቀ በአገራዊ ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ገለጻ አደረጉ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ገለጻ አደረጉ።

አቶ ደመቀ ከፍትህ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ጋር በመሆን ነው ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ለአደረጉ አምባሳደሮች እና ለቀጣናዊ እንዲሁም ዓለም ዓቀፋዊ ድርጅቶች ኃላፊዎች ገለጻ ያደረጉት፡፡

በገለፃቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ ስለሚካሄደው የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ማሻሻያዎች ላይ ያሉትን ወቅታዊ ሁኔታዎች አንስተዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን መንግስት የፕሪቶሪያው የሠላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር ቁርጠኛ መሆኑን በድጋሚ አረጋግጠዋል፡፡

እስካሁን ባለው ሁኔታም ሂደቱ አመርቂ ውጤት እንዳመጣ ተናግረዋል፡፡

በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ከተከሰተው ጦርነት በኋላ በፕሪቶሪያው የሰላም ሥምምነት መሠረት ወደ እርቀ ሠላም ለመድረስ የተካሄደው ሀገር አቀፍ ምክክርም በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነትን ማግኘቱንም ገልጸዋል፡፡

ሂደቱ እውነትን በማፈላለግ እና ቁርሾን በመርሳት ወደ እርቀ-ሠላም እንደሚያመራም ታምኖበታል ብለዋል፡፡

ግጭቱ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ፍትኅ የማስፈንና ተጎጂዎች እንዲካሱ የማድረግ ሥራም እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡

በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም የተገኙ ሲሆን÷ ለፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በሀገር አቀፍ ደረጃ በሽግግር ፍትኅ ፖሊሲ ማሻሻያ ላይ የሚመክረው ሀገር አቀፍ መድረክ ጉልኅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.