Fana: At a Speed of Life!

ከ8 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል የተባሉ ተከሳሾች በእስራትና በገንዘብ ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰበታ የጤና ጣቢያ ፕሮጀክት ውል ስምምነት ሳይደረግ ከ8 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል የተባሉ ተከሳሾች በእስራትና በገንዘብ ተቀጡ።

የቅጣት ውሳኔውን የወሰነው የኦሮሚያ ክልል የሸገር ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት ነው።

የቅጣት ውሳኔ የተወሰነባቸው ተከሳሾቹ 1ኛ የቀድሞ የሰበታ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊና የስራ ሂደት መሪ ጋዲሳ ሊንጀታ፣ 2ኛ የፕሮጀክት ክትትል ተቆጣጣሪ እና የሰበታ የኮንስትራክሽን ጽህፈት ቤት የቴክኒክ ኮሚቴ ኪሲ ሀይሉ፣ 3ኛ የሰራተኛና አስተዳደር የፋይናንስ ማዘጋጃ ቤት ባለሙያ ወርቁ ኃይለጊዮርጊስ፣ 4ኛ የሰበታ ማዘጋጃ ቤት የፋይናንስ ኢኮኖሚ ጽ/ቤት ባለሙያና የኮሚቴ ፀሀፊ ነበር የተባለው ቀኖ ባትሪ፣ 5ኛ የቀድሞ የአዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ መሀል መርካቶ ቅርጫፍ ስራ አስኪያጅ አስቻለው ሸዋ እና 6ኛ ተከሳሽ የሚንኮንግ ጀነራል ትሬዲንግ ሀ/የተ/የግ/ማህበር ወኪል እንዳሻው ሙላት ናቸው።

የኦሮሚያ ፍትህ ቢሮ የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ በተከሳሾቹ ላይ ሁለት ተደራራቢ ክስ አቅርቧል።

በዚህ መሰረት የሰበታ ጤና ጣቢያ የ40 ሚሊየን 450 ሺህ 650 ብር ፕሮጀክት የግንባታ ጨረታ በታህሳስ ወር 2009 ዓ.ም አሸንፎ ለነበረው ለማንኮንግ ጀነራል ትሬዲንግ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ወኪል የቦታ ርክክብ ባላደረገበትና ምንም ውል በሌለበት ሁኔታ ላይ ህግን ባልተከተለ መልኩ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ የመንግስት ሰራተኛ የሆኑ ተከሳሾች ቅድመ ክፍያ እንዲከፈለው ማስደረጋቸውን ዐቃቤ ህግ በክሱ ጠቅሷል።

በተለይም ተቋራጩ ከአዲስ ኢንተርናሽናል መሃል መርካቶ ቅርንጫፍ የቀድሞ ስራ አስኪያጅ ጋር በመመሳጠር የዋስትና ማስያዣ ምንም ነገር ባልተያዘበት እንዲሁም የባንኩን የአሰራር ደንቦች እና መስፈርቶችን ባላሟላበት ሁኔታ ላይ ዋስትና እንዳስያዘ በማስደረግ የግንባታ ቅድመ ክፍያ 8 ሚሊየን 130 ሺህ 176 ብር ከ95 ሳንቲም እንዲከፈለው መደረጉም በክሱ ዝርዝር ላይ ሰፍሯል።

በመንግስትና በህዝብ ሀብት ላይ ከ8 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ዐቃቤ ህግ በክሱ ላይ ጠቅሷል።

እንደአጠቃላይ ተከሳሾቹ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 ሀ እና አንቀጽ 33 እንዲሁም የሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 13 ንዑስ ቁጥር 2 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ የተሳትፎ ደረጃ ጠቅሶ የከባድ የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።

በአንደኛው ክስ የመንግስት ስራን በማያመች አኳኋን መምራት የሙስና ወንጀል ክስ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ተራ ቁጥር ለተጠቀሱ የመንግስት ሰራተኞች በሆኑት ተከሳሾች ላይ አቅርቧል።

በሁለተኛው ክስ ላይ ደግሞ በአዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ የቀድሞ የመሀል መርካቶ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅና በተቋራጩ ላይ ብቻ ነው ያቀረበው።

ከ1ኛ እስከ 4 ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች ችሎት ቀርበው ክሱ እንዲደርሳቸው ተደርጓል።

ቀሪ ሁለቱ ተከሳሾች ግን በተደጋጋሚ ተፈልገው ባለመገኘታቸውና ባለመቅረባቸው ምክንያት በሌሉበት ጉዳያቸው ሊታይ ችሏል።

በዚህ መልኩ ክሱ የደረሳቸው ተከሳሾች ወንጀሉን አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው የዕምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠታቸውን ተከትሎ ዐቃቤ ህግ የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎችን እና ሶስት የሰው ምስክሮችን በችሎት አቅርቦ የምስክርነት ቃል አሰምቷል።

ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ህግ ማስረጃን መርምሮ ተከሳሾቹ በተከሰሱበት አንቀጽ እንዲከላከሉ ብይን የሰጠ ሲሆን፥ በተገቢው መንገድ የዐቃቤ ህግ ማስረጃን መከላከል ባለመቻላቸው የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎባቸዋል።

የተከሳሾቹን የተለያዩ የቅጣት ማቅለያ አስተያየቶችን እና የዐቃቤ ህግን የቅጣት ማክበጃ አስተያየት የመረመረው ፍርድ ቤቱ ከአንደኛ እስከ አራተኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች እያንዳንዳቸው 4 አመት ከ5 ወራት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል።

ቀሪዎቹ 5ኛ እና 6ኛ ተከሳሾች ማለትም በአዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ የቀድሞ የመሀል መርካቶ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅና በተቋራጩ ላይ ደግሞ እያንዳንዳቸው በ6 አመት ከ6 ወራት ጽኑ እስራትና በ10 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ተወስኗል።

በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ የ5ኛ ተከሳሽ ማለትም የቀድሞ የአዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ የመሀል መርካቶ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ ዘመናዊ መኖሪያ ቤት ተሸጦ ያለአግባብ የተከፈለው 8 ሚሊየን 130 ሺህ 176 ብር ከ95 ሳንቲም ለመንግስት ገቢ እንዲሆን ተወስኗል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.