Fana: At a Speed of Life!

የሸገር ዳቦ ምርትን መልሶ ለመጀመር ሒደት ላይ መሆኑን የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሸገር ዳቦ ምርትን መልሶ ለመጀመር ሒደት ላይ መሆኑን የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ አስታውቋል፡፡

በቀን 1 ሚሊየን ዳቦ የሚያመርተው ድርጅቱ ምርቱ በመዲናዋ መሰራጨቱ ከቆመ ሁለት ወራት ተቆጥረዋል።

የሸገር ዳቦ ምርት የቆመበት ምክንያት ከስንዴ አቅርቦት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ችግሩንም ለመፍታት ከመንግስትና ከግል አቅራቢዎች ጋር እየተነጋገሩ እንደሚገኝ የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ኮሙኒኬሽን ኃላፊ ሰኢድ ሙሐመድ ተናግረዋል።

ተጠቃሚዎቹ በበኩላቸው ፥ የሸገር ዳቦ ምርት ዋጋው መጨመሩ እና የግራም መቀነስን በሚመለከት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

አቶ ሰኢድ ፥ በምላሻቸው የዳቦ ማሽኑ 80 ግራም የሚያመርት በመሆኑ የክብደት መዋዠቅ ሊፈጠር እንደማይችል ነው ያስረዱት።

ምርቱ ከመቆሙ በፊት የነበረው የስንዴ አቅርቦት ላይም ክፍተት በመኖሩ የስንዴ አቅራቢዎች ጨረታን በማውጣት የዳቦ ምርቱን ዳግም ለመጀመር ሒደት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተለይም በአነስተኛ ገቢ ያሉ የምርቱ ተጠቃሚዎች የተቋረጠው አቅርቦት ዳግም እንዲጀምር ነው ጥያቄያቸውን ያቀረቡት።

በፍቅረሚካኤል ዘየደ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.