Fana: At a Speed of Life!

የጠ/ሚኒስትሩ የሮም ቆይታ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራ ያከናወነችበት ነው – ቢልለኔ ሥዩም

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሮም ቆይታ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ልምድና ተሞክሮዋን ያጋራችበትና ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራ ያከናወነችበት መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሃላፊ ቢልለኔ ስዩም ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በጣሊያን ሮም በተካሄዱ በተባበሩት መንግስታት የምግብ ስርዓት ስብሰባና የዓለም አቀፍ የልማትና ፍልሰት ጉባዔ ላይ በመሳተፍ መልዕክት ማስተላለፋቸው ይታወሳል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ሃላፊ ቢልለኔ ስዩም ፥ ኢትዮጵያ የህገ-ወጥ ስደት መተላለፊያና መዳረሻ ሀገር መሆኗን ጠቅሰዋል።

ከዚህ አኳያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በጣሊያን ሮም በተካሄደው ዓለም አቀፍ የልማትና ፍልሰት ጉባዔ ላይ የችግሩን አሳሳቢነት በግልጽ አመላክተዋል ነው ያሉት።

በዚህም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በተለይ በሰሜንና ደቡባዊ የዓለም ክፍል ባሉ የዓለም ሀገራት መካከል ያለውን የልማት ልዩነት ማጥበብ እንደሚገባ መናገራቸውን ጠቁመዋል።

ለዚህ ደግሞ ለታዳጊ ሀገራት የእዳ ስረዛን ጨምሮ ድህነትን ለመቀነስ ለሚያከናውኗቸው ስራዎች ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ነው የገለጹት።

በእነዚህ ሀገራት የሚደረጉ የኢንቨስትመንት ስራዎች በዋናነት የወጣቶች ተጠቃሚነት ላይ ትኩረት ያደረጉ ሊሆኑ እንደሚገባም አመላክተዋል ብለዋል።

በሌላ መልኩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተመድ የምግብ ስርዓት ጉባዔ ላይ የኢትዮጵያን ተሞክሮ ማቅረባቸውን ሃላፊዋ ተናግረዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ በመስኖ ልማት፣ በሌማት ትሩፋት፣ በአረንጓዴ አሻራና በትምህርት ቤት ምገባ መርሃ-ግብር አማካኝነት የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ የምግብ ስርዓትን ለማሻሻል እየሰራች መሆኑን ማብራራታቸውን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይ በታዳጊ ሀገራት ያለውን የምግብ ስርዓት ችግር ለመፍታት አዲስና አካታች የፋይናንስ ድጋፍ ስርዓት እንዲኖር ሃሳብ አቅርበዋል ነው ያሉት።

በመድረኩም ፥ ኢትዮጵያ የተሻለ ተሞክሮ ማቅረቧን ጠቅሰው፤ ይህም ከተለያዩ ሀገራት ጋር በዘርፉ ያላትን ትብብር ለማጠናከር ያግዛል ብለዋል።

በሌላ መልኩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሮም ከተማ ለጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላ ያስቀመጡት ምሰለ ቅርጽ ኢትዮጵያ ጀግኖቿንና ታሪኳን ለዓለም ለማስተዋወቅ እድል የፈጠረ መሆኑን ነው የተናገሩት።

በሀገር ውስጥም መሰል ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

እንደ አጠቃላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሮም ቆይታ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ልምድና ተሞክሮዋን ያጋራችበትና ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራ ያከናወነችበት ነበር ብለዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.