Fana: At a Speed of Life!

በግጭት ጉዳት ለደረሰባቸው አካባቢዎች መልሶ ግንባታ የሚሆን የ60 ሚሊየን ዶላር በጀት ጸደቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ በግጭት ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች መልሶ የማልማት ፕሮጀክት አቢይ ኮሚቴ ለ2016 በጀት ዓመት በግጭት ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ለመልሶ ማቋቋመምና ግንባታ ተግባር የሚውል የ60 ሚሊየን ዶላር በጀት አጸደቀ፡፡

በቢሾፍቱ ከተማ በተካሄደው የአብይ ኮሚቴው ስብሰባ በግጭት ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች መልሶ ማልማት ፕሮጀክት የ2015 በጀት አመት አፈጻጸምና የ2016 በጀት አመት ዕቅድ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

በቀጣይ የ2016 ዓ.ም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በመወጣት ለህብረተሰቡ መቅረብ ያለባቸውን መሰረታዊ አገልግሎቶች ተግባራዊ ለማድረግ በተጠናከረ መልኩ መንቀሳቀስ እንደሚጠበቅባቸው አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

የታቀዱ ተግባራትን ለማከናወንም የ60 ሚሊየን ዶላር በጀት በፕሮጀክቱ አብይ ኮሚቴ አባላት መጽደቁን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

በስብሰባው የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሰመሪታ ሰዋሰውና የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ አለሚቱ ኡሙት ተገኝተዋል፡፡

በተጨማሪም የአብይ ኮሚቴው አባላት የትምህርት፣ የጤና፣ የውሃና ኢነርጂ፣ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትሮችና የአደጋ ስጋትና ዝግጁነት ተቋም ተወካዮች እንዲሁም የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ የሆኑት አምስት ክልሎች የአማራ፣ የአፋር፣ የኦሮሚያ፣ የቤንሻንጉል ጉምዝና የትግራይ የፕሮጀክት አስተባባሪዎች ተገኝተዋል፡፡

በግጭት ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች መልሶ የማልማት ፕሮጀክት በኢትዮጵያ መንግስትና በዓለም ባንክ መካከል በተደረገ ስምምነት በፈረንጆቹ ከ2022 ጀምሮ በ300 ሚሊየን ዶላር በጀት ለአምስት አመት ተግባራዊ የሚደረግ ፕሮጀክት ነው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.