Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በ2ኛው የተባበሩት መንግስታት የሥርዓተ ምግብ ጉባዔ የነበራት ተሳትፎ ስኬታማ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት የሥርዓተ ምግብ ጉባዔ የነበራት ተሳትፎ ስኬታማ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ።

በጉባዔው÷ በግብርናው ዘርፍ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ውጤታማ እንቅስቃሴዎችን የሚያሳዩ ልምዶች መቅረባቸውን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

በጉባዔው የተገኙት ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ግብርናን በማዘመን የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥና በሥርዓተ ምግብ ሽግግር ለማምጣት እየወሰደች ባለው የፖሊሲ እርምጃ ውጤቶች ዙሪያ ገለጻ ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የኩታ ገጠም እርሻን በማስፋፋት፣ ለሥነ ምኅዳሩ ተስማሚ የሆኑ የተሻሻሉ ዝርያዎችን፣ አነስተኛ ቴክኖሎጂዎችንና ሌሎች ግብአቶችን ለአርሶ አደሩ በማቅረብ የግብርና ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ለኢኮኖሚው ዕድገት የላቀ አበርክቶ እንዲኖረው እየሰራች መሆኑን አንስተዋል ነው ያሉት።

በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በበጋ መስኖ በተለይም በበጋ ስንዴ ምርት እና በሌማት ትሩፋት እየተገኙ ያሉ ውጤቶችን ለጉባዔው ማቅረባቸውን ገልጸዋል ነው ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግብርና ዘርፍ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማበረታታትም ሆነ በሥርዓተ ምግብ ሽግግር ለማድረግ አዲስና የተለየ የፋይናንስ ሞዴል ያስፋልጋል በማለት በአጽንኦት መናገራቸውንም ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) አንስተዋል፡፡

በአንደኛው ጉባዔ የተቀመጡ ዘላቂና አካታች የሥርዓተ ምግብ ሽግግር አቅጣጫዎች ጥሩ አፈጻጸም የታየባቸው ቢሆንም÷ በፋይናንስ አቅርቦት፣ በዓለም አቀፍ ትብብር፣ በአየር ንብረት ለውጥና በሰው ሰራሽ ምክንያት የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመቋቋም በትብብር በመስራት በኩል በርካታ ችግሮች መስተዋላቸውን አንስተዋል ብለዋል።

በመሆኑም ሀገሮች በሥርዓተ ምግብ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ በአነስተኛ እርሻ ሥር ነቀል ለውጥ በማምጣት ሽግግሩን ማፈጣን እንደሚገባቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአፅንኦት ማንሳታቸውን ለገሰ (ዶ/ር) ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

ለዚህም የሴቶችና የወጣቶች ተሳትፎን እንዲያሳድጉና ለግብርና ቴክኖሎጂ መስፋፋት እንዲሰሩ ጠይቀዋል ነው ያሉት።

በሌላ በኩል የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር በሰበሰቡት ዓለም አቀፍ የልማትና የፍልሰት ኮንፈረንስ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር÷ ሀገራዊ ዕድገትን ማፋጠን የስራ ዕድል ፈጠራን ለማስፋፋትና ድህነትን ለማቃለል፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና ፍልሰትን ለመቀነስ ወሳኝ እንደሆነ አንስተዋል ብለዋል።

እንዲሁም የፍልሰት መነሻ ምክንያቶችን ለይቶ ለመቅረፍ፣ ለስራ ዕድል ፈጠራ አዳዲስ የፋይናንስ ስርአት መዘርጋትና የክህሎት ግንባታን ማዕከል ያደረገ የስራ ስምሪት መተግበር እንደሚገባም መናገራቸውን ነው ጠቀሱት፡፡

በሌላ መልኩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጣሊያን ቆይታቸው በሮም ከተማ ለጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላ ያስቀመጡት ምሰለ ቅርጽ ኢትዮጵያ ጀግኖቿንና ታሪኳን ለዓለም ለማስተዋወቅ እድል የፈጠረ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በጉባዔው የተገኙት የግብርና እና የፕላንና ልማት ሚኒስትሮች በአንደኛው የተባበሩት መንግስታት የስርዓተ ምግብ ጉበኤ የተቀመጡ አቅጣጫዎች አፈፃፀም፣ በተገኙ ውጤቶችና ተግዳሮች ላይ የኢትዮጵያን የስራ እንቅስቃሴ ሪፖርት ማቅረባቸውን ተናገረዋል።

ዘላቂና አካታች የስርዓተ ምግብ ሽግግርን ለማሳካት በሚደረገው እንቅስቃሴ በፋይናንስ፣ በቴክኖሎጅ፣ በአመራር፣ በአየር ንብረት ለውጥ ማላመድ ዙሪያ ያሉ የኢትዮጵያ ልምዶች መቅረባቸውንም ገልጸዋል።
በየመድረኮቹ በነበሩ ውይይቶች ኢትዮጵያ በሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት የስርዓተ ምግብ ጉባዔ ደምቃ ሰንብታላች ነው ያሉት።

ከዚህ ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ልኡክ ከበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በማህበረ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ውጤታማ ውይይቶችን ማድረጉን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.