Fana: At a Speed of Life!

ኢመደአ የዲጂታላይዜሽን ልምዱንና እውቀቱን ለሌሎች አፍሪካ ሃገራት ለማካፈል ዝግጁ መሆኑን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) የቴክኖሎጂ ባለቤትነት እና የዲጂታላይዜሽን ልምዱንና እውቀቱን ለሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ለማካፈል ዝግጁ ነው ሲሉ የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ ገለጹ፡፡

አቶ ሰለሞን ሶካ ከአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ዋና ዳይሬክተር ፋታላህ ሲጂልማሲ ጋር አፍሪካ የቴክኖሎጂ ባለቤትነትን ማረጋገጥ በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል፡፡

በውይይታቸውም ኢመደአ በቴክኖሎጂ ባለቤትነት እና በዲጂታላይዜሽን ዙሪያ ያካበተውን አቅም፣ ልምድና እውቀት ለሌሎች የአፍሪካ ሃገራት አቻ ተቋማት ለማካፈል ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡

አፍሪካዊ ማንነትን የተላበሰ የዲጂታል ኢኮኖሚ በመገንባት እና የቴክኖሎጂ ባለቤነትን በማረጋገጥ የአፍሪካን ብልጽግና ማረጋገጥ ይቻላልም ነው ያሉት፡፡

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ዋና ዳይሬክተር ፋታላህ ሲጂልማሲ በበኩላቸው÷ አፍሪካ ከእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ለመውጣት በዋናነት የቴክኖሎጂ ባለቤትነትን ማረጋገጥና ከውጭ የቴክኖሎጂ ጥገኝነት መላቀቅ እንደሚገባት ገልጸዋል፡፡

ለዚህም÷ የኢትዮጵያ ተሞክሮ ለሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ጥሩ ምሳሌና መነሻ ሊሆን ይችላል ነው ያሉት፡፡

የኮሚሽኑ ዋና ዳይሬክተ የአስተዳደሩን የዲጂታል ኤግዚቢሽን ማዕከል እና የታለንት ልማት ማዕከልም የጎበኙ ሲሆን በጉብኝታቸው የተመለከቷቸው ሃገር በቀል የቴክኖሎጂ ምርትና አገልግሎቶች ወደ ሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ሊስፋፉ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የሁሉንም የአፍሪካ ሃገራት አቅምና ተሞክሮ በመደመር አፍሪካዊ የቴክኖሎጂ ባለቤትነትን ማረጋገጥ እንደሚገባም ማንሳታቸውን ከኢመደአ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.