Fana: At a Speed of Life!

ክልሎች ለነብዩ መሐመድ (ሰዐወ) የመውሊድ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች ለእስልምና እምነት ተከታዮች እንኳን ለ1 ሺህ 498ኛው የነብዩ መሐመድ (ሰዐወ) የመውሊድ በዓል አደረሳችሁ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የሐረሪ ክልል የመውሊድ በዓልን አስመልክቶ ባስተላለፈው መልዕክት÷ የመውሊድ በዓል ሲከበር እርስ በርስ የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴትን በሚያጠናክር መልኩ ሊሆን እንደሚገባም አስገንዝቧል፡፡

እንዲሁም የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው÷ በመልዕክታቸው ነብዩ መሐመድ (ሰዐወ) በእስልምና ሀይማኖት በነበራቸው አስተምህሮ የሰው ልጆች ያለ ዘርና ሃይማኖት ልዩነት የምድር ፍጡራን ሁሉ እኩል መሆናቸውን ሲያስተምሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

“ነብዩ መሐመድ ለዓለም እዝነትና ደግነትን ያስተማሩ እንደመሆናቸው እኛም ለሌሎች ወገኖች እዝነትንና ደግነትን በማሳየት አርአያነታቸውን ልንከተል ይገባል” ብለዋል።

በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ÷ ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች ለ1 ሺህ 498ኛው የመውሊድ በዓል እንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር፣ የደሰታ፣ የመረዳዳትና የአብሮነት እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን በማህበራዊ ትትስር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በዓሉን አስመልክቶ ባስተላለፈው መልዕክት÷በዓሉ ፈጣሪን በመለመን፣ በጸሎት፣ ተካፍሎ በመብላትና በሌሎች በሚያስመሰግኑ መልካም ሥራዎች በእምነቱ ተከታዮች እንደሚከበር ገልጿል፡፡

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው÷ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር በህዝቦች መካከል ያለውን አንድነት በሚያጠናክር መልኩ የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት፣ በመደጋገፍና በመተሳሰብ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

እንዲሁም የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ÷የመውሊድ በዓል ሲከበር የሙስሊሙ ማህበረሰብ ሀይማኖታዊ አስተምህሮ የሆኑትን ሠላም ወዳድነት፣ እውነተኛነት፣ አዛኝነት እና መተባበር እሴቶችን በጠበቀ መልኩ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.