Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በሲቪል አቪየሽኑ ዘርፍ ለቀጣናው ድጋፍ ማድረግ የሚያስችላትን ሥምምነት ፈጸመች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በሲቪል አቪየሽኑ ዘርፍ ለቀጣናው ድጋፍ ለማድረግ አዲስ የማስተግበሪያ ሥምምነት ከዓለም አቀፉ የሲቪል አቪየሽን ድርጅት ጋር ፈጸመች፡፡

ኢትዮጵያ ሥምምነት ላይ የደረሰችው ድርጅቱ ባስቀመጣቸው መርሆዎች እና ደረጃ መሠረት የአተገባበር ድጋፍ ለማድረግ ነው፡፡

በሥምምነቱ መሠረት የቀጣናው የአቪየሽን ዘርፍ ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ አስተማማኝ እና ዘላቂ ልማት እንዲያስመዘግብ ወሳኝ አሥተዳደራዊ ሚና ትጫወታለች ተብሏል፡፡

ሥምምነቱ ከምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ የድርጅቱ ቀጣናዊ ጽኅፈት ቤት ጋር በመተባበር፥ በአቪዬሽኑ ዘርፍ የሚካሄዱ ፕሮጀክቶችን በትብብር ለማሳለጥ ወሳኝ መንገድ ይከፍታል መባሉን ከድርጅቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የዓለም አቀፉን የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የአቅም ልማትና ትግበራ ቢሮ ከሚሰጠው የትግበራ ድጋፍ አገልግሎት ጋር በተጣጣመ መልኩ የሚተገበር መሆኑም ነው የተገለጸው።

በዚህም የልምድ ልውውጥ ፣ የፕሮጀክት አሥተዳደር፣ የሥልጠና ፓኬጆችን ማዘጋጀት እንዲሁም ከግዢ ጋር የተገናኙ የትግበራ ድጋፍ ምርቶችን እና አገልግሎቶችን ማቅረብን ያጠቃልላልም ነው የተባለው።

ሥምምነቱን የዓለም አቀፉ የሲቪል አቪየሽን ድርጅት ዋና ፀኃፊ ሁዋን ካርሎስ ሳላዛር እና የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው መንግስቴ ተፈራርመዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.