Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያውያን ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት የጀመሩትን ተሳትፎ አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል – አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያውያን ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት የጀመሩትን ተሳትፎ አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ሲሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ጥሪ አቀረቡ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአንድ ዓመት ከሰባት ወራት የሥራ እንቅስቃሴ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ከፍትኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ዛሬ ውይይት ተደርጎበታል።

በውይይቱም የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር የእስካሁን የሥራ አፈጻጸምን ያቀረቡ ሲሆን፤ በዚህም በአምስት ክልሎችና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች የተሳታፊዎች ልየታ መከናወኑን ገልጸዋል።

በውይይቱ የተሳተፉት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ፤ ምክር ቤቱ ኮሚሽኑን ገለልተኛ ተቋም አድርጎ ማቋቋሙን አስታውሰዋል።

በዚህም ኮሚሽኑ ዕቅድና ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ሥራዎችን በአራት ምዕራፍ ማለትም የቅድመ ዝግጅት፣ የዝግጅት፣ የትግበራና የማጠቃለያና የግብረ መልስ በሚል ከፋፍሎ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

እስካሁን ባለው ሂደትም በቅድመ ዝግጅትና በዝግጅት ስራዎች ለምክክሩ መሰረት የሚጥሉ ተግባራት በጥሩ ሁኔታ መከናወናቸውን ገልጸዋል።

ለአብነትም በአምስት ክልሎችና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች ከወረዳ ጀምሮ የተሳታፊና የአስተባባሪ እንዲሁም የአጀንዳ ልየታ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።

የፀጥታ ችግር ባለባቸው እንደ አማራና ኦሮሚያ ባሉ አካባቢዎች በቀጣይ ምክር ቤቱና የምክክር ኮሚሽኑ ቀሪ ሥራዎችን እንደሚያከናውኑ ገልጸው፤ ምክር ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡

ሀገራዊ ምክክር የሁሉም ኢትዮጵያውያን መሆኑን በማንሳት አጀንዳ አፍላቂውም ምክክር አድራጊውም ህዝብ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

መንግስት ለምክክሩ ስኬታማነት ድጋፍ የማድረግ እንጂ አጀንዳ ሰጪ አይደለም ያሉት አፈ ጉባኤው፤ ህዝብ ተመካክሮ የሚደርስባቸውን ውሳኔዎች መንግስት ይቀበላል ብለዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ በዚህ ዓመት አጋማሽ እንደሚካሄድ በመጠቆም ምክክሩ በስኬት እንዲጠናቀቅ መንግስት አስተማማኝና ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር ባለፈ ሰላምን የማስፈን ስራን ጨምሮ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት።

በመሆኑም መላው ኢትዮጵያውያን ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት የነቃ ተሳትፎና ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.