Fana: At a Speed of Life!

የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ለሚከናወኑ የለውጥ ስራዎች ድጋፉን እንደሚያጠናክር ገለጸ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ለሚገኙ የለውጥ ስራዎች የሚያደርገው ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የህብረቱ የዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒላይነን አስታወቁ፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ከአውሮፓ ሕብረት የዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒላይነን ጋር ተወያይተዋል።

ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)÷ የአውሮፓ ሕብረት ለኢትዮጵያ ቁልፍ ስትራቴጂካዊ አጋር መሆኑን ገልጸው÷ እስካሁን ለኢትዮጵያ ላደረገው ትብብር ምስጋና አቅርበዋል።

የመካከለኛ ዘመን የሶስት ዓመቱን የኢንቨስትመንት እቅድ እንዲሁም የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ሁለትን ይዘቶች አስመልክተውም ገለጻ አድርገዋል፡፡፡

ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒላይነን÷ የአውሮፖ ህብረት ከኢትዮጵያ ጋር የሚያከናውናቸውን የትብብር ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

ህብረቱ በአየር ንብረት ለውጥ መከላከልና ግብርና ስራዎች፣ ብዝሃ ሕይወት ጥበቃ፣ አረንጓዴ ልማት፣ አካባቢ ጥበቃና ታዳሽ ኃይል ልማት፣ ለሰው ኃይል ልማት፣ በጤና፣ በመልካም አስተዳደር፣ ሰላም ግንባታና የዴሞክራሲ ልማት ስራዎች ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በትብብር እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒላይነን አዲስ አበባ ከሚገኙ የህብረቱ ዲፕሎማቶች ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም÷ ዲፕሎማቶች በኢትዮጵያ በሚያከናውኗቸው ስራዎች ዙሪያ ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡

የአውሮፕ ህብረትና ኢትዮጵያ ያላቸውን ስትራቴጂያዊ ትብበር ይበልጥ ለማጠናከር በቅንጅት እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡

የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ለሚገኙ የለውጥ ስራዎች የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.