የፓሌርሞ ኮንቬንሽን ሚኒስትሮች ኮንፈረንስ ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የተሳተፈችበት 20ኛው የፓሌርሞ ኮንቬንሽን ሚኒስትሮች ኮንፈረንስ ጉባኤ ተጠናቋል፡፡
በርካታ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በተገኙበት በዚህ ኮንፈረንስ በሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዱአለም የተመራ የኢትዮጵያ ልኡካን ቡድን ተሳትፏል፡፡
በኮንፈረንሱ በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና ህገ-ወጥ ስደተኞች ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄዱ ተመላክቷል፡፡
በዚህ ወቅት የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዷለም÷ ኢትዮጵያ ህገ-ወጥ ስደትና ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመቆጣጠር የወሰደቻቸውን የፖሊሲ ማእቀፎች፣ ተቋማዊ አደረጃጀቶች እና የማስተካከያ እርምጃዎችን በመድረኩ አንስተዋል፡፡
አክለውም ኢትዮጵያ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗን መግለጻቸውን የሰላም ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡