Fana: At a Speed of Life!

የኢሬቻ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ የፀጥታ አካላት ወደ ስራ መግባታቸውን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ገለጸ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ እና የሆራ አርሰዲ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ የፀጥታ አካላት ቅድመ ዝግጅታቸውን አጠናቀው ወደ ስራ መግባታቸውን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ፡፡

ግብረ ኃይሉ የአዲስ አመት፣ የመስቀልና የመውሊድ በዓላት አከባበርን በመገምገም÷ የኢሬቻ በዓል ቅድመ ዝግጅትን አስመልክቶም ውይይት አድርጓል፡፡

በውይይቱ ላይ እንደተገለጸው÷ መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም የሚከበረው የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ የፀጥታ ስራው በቴክኖሎጂ ይደገፋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ዘርፍ ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ እንደገለጹት÷ የፀጥታ አካላት አመራሮችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት በመስራታቸው ሰሞኑን የተከበሩ በዓላት በሰላም ተጠናቀዋል፡፡

ፀረ-ሰላም ኃይሎች ከዚህ ቀደም የተከበሩ በዓላትን ለማወክ መንቀሳቀሳቸውን ጠቁመው÷ በፀጥታ ተቋማትና ጉዳዩ በሚመለከታቸው አካላት ጥረት ሴራቸው መክሸፉን አስታውሰዋል፡፡

በኢሬቻ በዓላት አከባበር ላይም ጸረ-ሰላም ኃይሎች የሚያስቡትን ፀጥታ የማደፍረስ ተግባራቸውን ለመፈፀም ወደ ኋላ እንደማይሉ የፀጥታ ኃይሉ በልዩ ልዩ ማስረጃ አረጋግጧል ነው ያሉት፡፡

በመሆኑም የጸጥታ ኃይሉ ሴራቸውን እየተከታተለ እያከሸፈባቸው ነው ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ በበኩላቸው÷ በኢሬቻ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ለማሳደር የሚደረግ ህገወጥ ተግባራትን የጸጥታ አካላት እንደማይታገሱት ተናግረዋል፡፡

የኢሬቻ በዓል ሰላማዊ ሆኖ እንዲከበር ለወንጀል መከላከል ተግባር ልዩ ትኩረት መሰጠቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው አስታውቀዋል፡፡

በበዓሉ ላይ ከባህላዊ አከባበሩ ተቃራኒ የሆኑ ተግባራት፣ ግጭት ቀስቃሽ የሆኑ ጽሑፎችና መልዕክቶችን መያዝ ክልክል ነው ተብሏል፡፡

በዓሉ ወደ ሚከበርበት ስፍራ የሚመጡ ታዳሚዎች ለጋራ ደህንነት ሲባል ፍተሻ መኖሩን ተገንዘበው ትብብር እንዲያደርጉ የጋራ ግብረ ኃይሉ ጠይቋል፡፡

ህብረተሰቡ ለሰላም እንቅፋት የሆኑ አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙት በ011-1-26-43-59፣ 011-5-52-63-02/03፣ 011-5-52-40-77፣ 011-5-54-36-78 እና 011-5-54-36-81 እንዲሁም በ987፣ 991 እና 816 ነፃ የስልክ መስመሮች ጥቆማ በመስጠትና አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ግብረ ኃይሉ ጥሪ አቅርቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.