Fana: At a Speed of Life!

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ በአፖስቶ ማዕከል የመስክ ምልከታ አደረገ

 

አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ በሲዳማ ክልል በቀድሞ የደቡብ ፖሊስ ማሰልጠኛ ኮሌጅ ልዩ ስሙ አፖስቶ ማዕከል የመስክ ምልከታ አድርጓል፡፡

የመርማሪ ቦርዱ አባላት ምንም እንኳ ቦታው በአስቸኳይ ጊዜ መምሪያ እዝ ስር የሚካተት ባይሆንም በዜጎች ላይ ማንነት ተኮር እስርና የሰብዓዊ መብት ጥሰት አለ በሚል የደረሱ ጥቆማዎችን መሰረት በማድረግ ነው ምልከታ ያደረጉት፡፡

በቦታው በመገኘት ለማረጋገጥ በተደረገ ምልከታም በሲዳማ ክልል የይርጋለም ከተማ አፖስቶ ወይንም የደቡብ ፖሊስ ኮሌጅ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ አማካኝነት በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች አለመኖራቸውን ገልጿል።

ቦርዱ በዋናነት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር ተያይዞ በማዕከሉ ማንነትን መሰረት ያደረገ የጅምላ እስርና በእስረኞችም ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመ ነው የሚለውን ጥቆማ እንደ ግብዓት መጠቀሙ ተመላክቷል፡፡

በዚህም መሰረት የታሳሪዎችን ስም ዝርዝር፣ የሰብዓዊ አያያዝ ሁኔታ፣ የተጠርጣሪዎችን ብዛትና የተያዙበትን ምክንያት እንዲሁም ከተጠርጣሪዎች ጋር ውይይት ለማድረግ በማለም ወደ ስፍራው መንቀሳቀሱ ተጠቁሟል፡፡

ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት በቦታው ምንም አይነት ተጠርጣሪዎችን ማግኘት አለመቻሉን የቦርዱ አባላት ገልጸዋል።

የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ነጃት ግርማ (ዶ/ር)÷ በስፍራው ተገኘወተው ማዕከሉን ተዘዋውረው መመልከታቸውን ገልጸዋል።

ነገር ግን በምልከታቸው ወቅት በማሰልጠኛ ማዕከሉ አንድም ተጠርጣሪ ግለሰብ ለማግኘት አልቻልንም ብለዋል።

ከሲዳማ ክልል የፀጥታ ሃላፊዎች፣ ከፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ የደቡብ ኢትዮጵያ ወንጀል ምርመራ ክላስተር ሃላፊዎችና የአፖስቶ የፖሊስ ማሰልጠኛ ኮሌጅ ሃላፊዎች ጋር መወያየታቸውንም አንስተዋል፡፡

በውይይቱም ከዚህ በፊት በማዕከሉ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ የታሰረ አንድም ተጠርጣሪ እንዳልነበረ ገልጸውልናል ሲሉ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ከወር በፊት ወደ ኮሌጁ ከአዲስ አበባ የመጡ ግለሰቦች እንደነበሩ ሃላፊዎቹ መግለጻቸውን ነው የተቀሱት፡፡

ግለሰቦቹ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር ግንኙነት በሌለው አዲስ አበባን ማዕከል ያደረገ ፀጥታ ስጋት በመፈጠሩ አስቀድሞ የወንጀል ስጋቶችን ለመቀነስና ለመከላከል ሲባል የተወሰኑ ምልክት የታየባቸውን የተለያየ የብሔር ስብጥር ያላቸውን ግለሰቦች በመደበኛ ወንጀል መከላከል ስርዓት በተሃድሶ ስልጠና ተመክረው እንዲመለሱ የመጡ እንደነበሩ መገለጹን አንስተዋል፡፡

ግለሰቦቹ አጫጭር የተሃድሶና የግንዛቤ መፍጠሪያ ስልጠናዎችን እንዲወስዱ በማድረግ ወደመጡበት አካባቢ እንዲመለሱ እንደተደረገ መጠቆሙን የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.