Fana: At a Speed of Life!

ሀገር አቀፍ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን መረጃ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ሀገር አቀፍ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን መረጃዎች ለማደራጀትና ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በስምምነቱ ወቅት እንዳስታወሱት÷ ሚኒስቴሩ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን ሲያስጀምር የመረጃ እጥረት ትልቅ ችግር ሆኖበት ነበር።

ይህንን ችግር ለመፍታትም ወዲያው ወደ ስራ እንደተገባ ገልጸው፤ አሁን ላይ ከዓለም ባንክ በተገኘ ድጋፍ ስራውን ለማስጀመር መብቃታቸውንም ገልጸዋል።

ታማኝ የሆነና ወቅታዊ መረጃ አምራች ኢንዱስትሪውን በእጅጉ እንደሚደግፍም አንስተው፤ ለኢንዱስትሪዎቹ የሚገነቡ መሰረተ ልማቶች በመረጃ ላይ የተመሰረቱ ሲሆን ውጤት እንደሚመጣ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዎች ተበታትነው የሚገኙ በመሆኑ በትስስር ለመስራት መረጃው አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል።

በዚህ የመረጃ ስርዓት ውስጥ የማይካተቱ ኢንዱስትሪዎች ምንም አይነት አገልግሎት ከመንግስት ማግኘት እንደማይችሉም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በቀጣይም የዲጂታል ግብይት ስርዓትን ለመዘርጋት ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር እየሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ታማኝ የሆነና ወቅታዊ መረጃዎችን በማቅረብ ለፖሊሲዎችና ለውሳኔዎች አጋዥ እንዲሆኑ ቅድሚያ ሰጥተን እንሰራለን ብለዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያስጀመረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄም በይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን የበኩላቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል።

በዘመን በየነ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.