Fana: At a Speed of Life!

አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ለኢሬቻ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 25 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ለኢሬቻ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ባስተላለፉት መልዕክት የሰላም፣ የፍቅር፣ የእርቅ እና የአንድነት ማሳያ ለሆነው የኢሬቻ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ ብለዋል።

ኢሬቻ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሀብት ከመሆኑም ባሻገር አንድነትን የሚያጎለብት ታላቅ በዓል እንደሆነ ገልፀዋል።

ኢሬቻ ከልዩነት ይልቅ አንድነት የሚንፀባረቅበት፣ የምስጋና፣ የእርቅና ሠላም በዓል መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

የኢሬቻ በዓልን ስናከብር ባህልና ወጉን በጠበቀና በሚያጠናክር መልኩ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፉ በማድረግ ሊሆን ይገባልም ነው ያሉት።

በኢሬቻ በዓል የኦሮሞ ህዝብ ለፈጣሪ ምስጋና ለማቅረብ በአንድነት ከመሰባሰቡ በፊት የተጣሉ የሚታረቁበትና ይቅር የሚባባልበት በዓል ነውም ብለዋል በመልዕክታቸው።

ኢሬቻ ካለው የሰላምና አንድነት እንዲሁም የተስፋና ልምላሜ ዕሴት አንጻር ያለውን ጉልህ ሚና ለትውልድ ለማሸጋገር መጠበቅና መንከባከብ እንደሚገባም አስታውቀዋል።

የኢሬቻ በአል ተሳታፊዎችም አንድነትን፣ ወንድማማችነትን እና እህትማማችነትን በማጎልበት ሰላም በሚያረጋገጥ መልኩ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም መልዕክት አስተላልፈዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.