Fana: At a Speed of Life!

ይህን ክፉ ጊዜ ማለፍ የሚቻለው በመተጋገዝና በመተሳሰብ ነው- ወ/ሮ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ይህን ክፉ ጊዜ ማለፍ የሚቻለው በመተጋገዝና በመተሳሰብ መሆኑን የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ገለፁ።

በኦሮሚያ ክልል የአርሲ ዞን ተወላጆች ከተለያዩ አካላት ያሰባሰቡትን የ20 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ቁሳቁስ በዞኑ ሰባት ወረዳዎች ለሚገኙ የተቸገሩ ሰዎች አበርክተዋል።

ድጋፉ በኮቪድ 19 ምክንያት የሚመጣውን የኢኮኖሚ ጫና ለመቀነስ የሚያግዝ መሆኑም ተገልጿል።

ድጋፉን ያስተባበሩት የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፣ የብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ስቪክ ማኅበራት ጉዳዮች ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ዓለሙ ስሜ እንዲሁም የፌዴራል የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ኮሚሽነር ጀማል አባሶ ናቸው።

አስተባባሪዎቹ ከተለያዩ አካላት ያስባሰቡት ጥቅል ድጋፍም ግምቱ 20 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ዱቄት፣ ዘይት፣ ደረቅና ፈሳሽ ሣሙና፣ ሳኒታይዘር፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛና የተለያዩ ልብሶችን ያካተተ ነው።

የአካባቢው ተወላጆች ይህንኑ ድጋፍ በዞኑ መርቲ ወረዳ አቦምሳ ከተማ ተገኝተው ድጋፉን ለሚሹና ለወረዳ አስተዳደሪዎች አስረክበው፤ የአካባቢው ሙስሊሞችንም አስፈጥረዋል።

ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ከድጋፉ በኋላ እንደተናገሩት ይህን ክፉ ጊዜ ማለፍ የሚቻለው በመተጋገዝና በመተሳሰብ ሲሆን ነው።

ወቅቱ ከባድና ፈታኝ መሆኑ ታውቆ ሁሉም ወረርሽኙ በአገር ላይ እያደረሰ ያለው ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመቋቋም መተባበር አለበት ብለዋል።

ድጋፉ በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ እንዲሆን በየአካባቢው እንደ አቅሙ ሊደግፍና ሊረዳ ይገባል ብለዋል።

”ይህ ወቅት አንዱ ለሌላው የሚኖርበት ጊዜ በመሆኑ ሕዝቡ ልዩነትን የሚሰብኩትን ሳይሰማ አንድነቱን ሊያጠናክር ይገባል” ያሉት ደግሞ የብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ስቪክ ማኅበራት ጉዳዮች ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ዓለሙ ስሜ ናቸው።

እርሳቸው እንዳሉት የተወሰኑ አካላት በዚህም ጊዜ ልዩነት ላይ ያተኮሩ በመሆኑ ሕዝቡ ለእነዚህ አካላት ጆሮውን መስጠት የለበትም።

ችግሩን ማለፍ የሚቻለውም በአንድነት፣ በመዋደድ፣ በመተሳሰብና በመተጋገዝ በመሆኑ ሁሉም ትኩረቱን እዚህ ላይ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የአርሲ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጀማል ዓሊዩ በበኩላቸው ድጋፉ ለበርካታ ችግሮች የሚደርስና ፋይዳውም የላቀ መሆኑን ተናግረዋል።

የአካባቢው ተወላጆች አስበውና አስታውሰው ሕዝባቸውን ለማገዝ ስለመጡም ትልቅ ምሥጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

በዕለቱ ድጋፉ የተደረገላቸው የአካባቢው ነዋሪዎችም ለተደረገላቸው ሁሉ ምሥጋናቸውን ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.