Fana: At a Speed of Life!

የካይዘን ልህቀት ማዕከል መቋቋም ለእውቀት ሸግግር የጎላ ሚና እንደሚጫዎት ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የካይዘን ልህቀት ማዕከል በኢትዮጵያ መቋቋሙ በአፍሪካውያን መካከል የእውቀት ሸግግር እንዲኖር ከፍተኛ ሚና አለው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የተገነባው የካይዘን ልህቀት ማዕከል በዛሬው እለት ለምርቃት ተመርቋል፡፡

በምርቃ ስነስርዓቱ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበልና በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮን ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

አቶ ደመቀ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ÷የካይዘን ልህቀት ማዕከሉ በኢትዮጵያና በጃፓን መንግስት ትብብር በ 27 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር መገንባቱን ገልጸዋል፡፡

የጃፓን መንግስት በኢትዮጵያ በሰው ሃብት ልማት ግንባታ ላይ እያደረገ ላለው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የልህቀት ማዕከሉ ውጤታማ የሰው ሃብት ልማት በማሳለጥ እንደሀገር የተያዘውን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት ከፍተኛ ድርሻ አለውም ነው ያሉት፡፡

የካይዘን ልህቀት ማዕከሉ በኢትዮጵያ መቋቋም በአፍሪካውያን መካከል የእውቀት ሸግግር እንዲኖር ሚናው ከፍተኛ እንደሚሆንም ገልጸዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው ÷ ካይዘን ማለት እንደ አገርም ሆነ እንደ ግለሰብ የማያቋርጥ ለውጥ ማረጋገጥ ማለት ነው ብለዋል።

በመሆኑም ፍልስፍናው በኢትዮጵያ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ወዲህ በአምራች ኢንዱስትሪዎችና በአገልግሎት ሰጭ ተቋማት በርካታ ለውጦች ተመዝግበዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በኢትዮጵያ የካይዘን ፍልስፍና ተግባራዊ መሆን የጀመረው በ2009 የዘመን ቀመር መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳድር ኢቶ ታካኮ ናቸው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.