Fana: At a Speed of Life!

የእንግሊዝ ንጉሳዊ ቤተሰብ አባል ሶፊ ሄሌን ራይስ ጆንስ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የእንግሊዝ ንጉሳዊ ቤተሰብ አባል ሶፊ ሄሌን ራይስ ጆንስ ዛሬ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕን ጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰውና ሌሎች የአየር መንገዱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

በቆይታቸውም የአየር መንገዱን የአቪዬሽን ዩኒቨርሲቲና የአውሮፕላን ጥገና ማዕከሉን ጉብኝተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው በዚሁ ጊዜ ሶፊ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሚሰጠው አገልግሎት ደስተኛ መሆናቸውንም ለማወቅ ተችሏል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ እንግሊዝ አገር መብረር ከጀመረ 50 ዓመታትን ያስቆጠረ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ትስስር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በዚህ ረገድ የዛሬው የእንግሊዝ ንጉሳዊ ቤተሰብ አባል ሶፊ ጉብኝት ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል።

ጉብኝቱ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ትብብር ይበልጥ እንደሚያጠናክረውም እምነታቸውን ገልጸዋል።

ሶፊ ሄሌን ራይስ ጆንስ በበኩላቸው የአፍሪካ ኩራት የሆነውን የኢትዮጵያ አየር መንገድን በመጎብኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመው፤ አየር መንገዱ ስኬታማ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ሶፊ ሄሌን ራይስ ጆንስ የእንግሊዝ ንጉስ ቻርለስ ሦስተኛ ታናሽ ወንድምና የስኮትላንድ ከተማ ‘ኤዲንቦሮው’ መስፍን ልዑል ኤድዋርድ ባለቤት ናቸው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.