Fana: At a Speed of Life!

የጃፓን ዓለምአቀፍ ትብብር ድርጅት በኢትዮጵያ ጀማሪ የቴክኖሎጂ ስራዎችን እንደሚያግዝ ገለፀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ድርጅት (ጂ አይ ካ) የኢትዮጵያን ጀማሪ ቴክኖሎጂ ሥነምህዳርን በማገዝ የግል ሴክተሩን ለማጠናከር እንደሚሰራ ገለጸ፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂና ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶክተር)  በጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ድርጅት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢሞቶ ሳቺቾ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸው ሚኒስትሩ ከጀማሪ የንግድ ስራ ባለድርጅቶች ጋር  በሰኔ ወር በጃፓን ተገኝተው ጠቃሚ ልምድ ማግኘታቸውን አስታውሰዋል፡፡

በቀጣይም በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ማዕከል፣ በሞዴል የጀማሪ ከተማ ግንባታ እና በተባባሪነት ዘርፎች ከጃፓን የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ጋር በቅርበት ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ እንደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የጂ አይ ካ ትብብር ተቀዳሚ መዳረሻ እንድትሆን እንፈልጋለን ያሉት ሚኒስትሩ፥ በአዲስ አበባ ከተማ ሞዴል የስታርትአፕ ከተማ ለመገንባት አስቻይ ሁኔታ እንዲኖር በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ጂ አይ ካ የጃፓን ባለሃብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን በኢትዮጵያ ምቹ ሥነምህዳር ላይ እንዲያውሉ ለማድረግ ትብብሩን አጠናክሮ  እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ድርጅት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢሞቶ ሳቺቾ በበኩላቸው÷ ጃፓን የግሉን ዘርፍ በማጠናከርና የኢንቨስትመንት ትብብርን ለማስፋት ቅድሚያ ከምትሰጣቸው ሀገራት አንዷ ኢትዮጵያ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

አክለውም ጂ አይ ካ  በጀማሪዎች ሥነምህዳር፣ በግል ዘርፍ የልማት ትብብር መስኮች፣ በወጣቶች ተሰጥኦ ማጎልበትና በሰው ተኮር የልማት ፕሮግራሞች በትብብር ለመስራት እቅድ እንዳለው ነው ያስረዱት።

በተጨማሪም ስታርታፕን በመደገፍ ኢትዮጵያን ሞዴል አድርገን ለመስራት ትብብራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ማለታቸውን ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.