Fana: At a Speed of Life!

ቅበት ከተማ በነበረው ግጭት የተፈናቀሉትን ለመመለስናችግሮችን ለመፍታት መግባባት ላይ ተደረሰ

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በስልጤ ዞን ቅበት ከተማ በነበረው ግጭት የተፈናቀሉትን ለመመለስና ችግሮችን በዘላቂነት በጋራ ለመፍታት መግባባት ላይ መደረሱን የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለፀ።

ጉባኤው ከስልጤ ዞን አስተዳደር ጋር በመተባበር በቅበት ከተማ የተከሰተውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ በዘላቂነት ለመፍታት ያለመ ሕዝባዊ የምክክር መድረክ አካሂዷል።

የጉባኤው ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ የምክክር መድረኩን አስመልክተው እንደተናገሩት፤ ጉባኤው የተፈጠረውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ኮሚቴ አዋቅሮ ሲሰራ ቆይቷል።

በኮሚቴው ጥናት መሰረት የነበሩ ችግሮች ተለይተው ከህብረተሰብ ተወካዮች ጋር ምክክር እንደተደረገባቸውም ነው ያስረዱት።

ተፈናቃይ ወገኖችን ጨምሮ ከሁሉም ማህበረሰብ ክፍል ተወካዮች እና ከመንግሥት መዋቅር አካላት ጋር ለሁለት ቀናት ውይይት መካሄዱንም ገልፀዋል።

በዛሬው የምክክር መድረክም የተፈጠረውን ችግር ፈትቶ ወደነበረበት ሰላማዊና የአብሮነት ኑሮ ለመመለስ ሁሉም ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል ነው ያሉት።

ለግጭት መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን በጋራ ለመፍታት ኮሚቴ መቋቋሙን ገልፀው፤ የተፈናቀሉ ዜጎችን ከአንድ ሳምንት በኋላ እንዲመለሱ የሚያስችል መግባባት ላይ መደረሱን እንደተናገሩ ኢዜአ ዘግቧል።

የግጭት መባባስ መንስኤ የሆኑ ጥፋተኞች፣ ዜጎችን ያፈናቀሉና ንብረት ያወደሙ ሰዎች በሕግ ተጠያቂ እንደሚደረጉና የወደሙ ቤቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ በኮሚቴው አስተባባሪነት በጋራ እንደሚገነቡም ጠቁመዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.