Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ለስደተኞችና ተቀባይ ሀገራት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠየቀች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተመድ የስደተኞች ኤጀንሲና አጋሮች ጫና እና ኃላፊነትን በመጋራት መርሕ ለስደተኞችና ተቀባይ ሀገራት ተጨባጭ ድጋፍ እንዲያደርጉ ኢትዮጵያ ጥሪ አቅረበች፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽነር 74ኛው የሥራ አስፈጻሚዎች ስብሰባ በስዊዘርላንድ ጄኔቫ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩም በስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ጠይባ ሐሰን የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ እየተሳተፈ ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያ የስደተኞች ጥበቃ እና ራስን መቻል ላይ እየተሠሩ የሚገኙ ሥራዎችን አስመልክቶ የተመዘገቡ ስኬቶች፣ ያጋጠሙ ፈተናዎች እና በቀጣይ የሚከናወኑ ተግባራትን ወ/ሮ ጠይባ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ አንድ ሚሊየን የሚጠጉ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎችን በማስተናገድ ከባድ ኃላፊነት እየተወጣች መሆኗንም ዋና ዳይሬክተሯ አንስተዋል፡፡

በቀጠናው ባለው ግጭት ወደ ሀገሪቱ እየገቡ ካሉ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ጋር ተያይዞ የተከሰተውን ሁኔታ መስመር ለማስያዝ የተቀናጀ የቀውስ ምላሽ ያሻል ብለዋል፡፡

የተመድ የስደተኞች ኤጀንሲ እና አጋሮች ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበው÷ በቀጣይም ጫና እና ኃላፊነትን በመጋራት መርህ ለስደተኞችና ተቀባይ ሀገራት ተጨባጭ አጋርነት እንዲያሳዩ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ልዑክ ከስብሰባው ጎን ለጎን ከተለያዩ ባለድርሻዎችና አጋር አካላት ጋር ዘርፈ-ብዙ ውይይቶችን እያደረገ እንደሚገኝም የአገልግሎቱ መረጃ አመላክቷል፡፡

ልዑኩ ከአሜሪካ የህዝብ፣ ስደተኞችና ፍልሰት ድርጅት ልዑክ፣ ከተመድ የስደተኞች ኤጀንሲ የኦፕሬሽን ረ/ኮሚሽነር ራዑፍ ማዡ እንዲሁም ከምስራቅ፣ የአፍሪካ ቀንድና ታላላቅ ሐይቆች ቀጠናዊ ቢሮ ዳይሬክተር ማማዱ ዲያን ባልዴ ጋር በጋራ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.