Fana: At a Speed of Life!

ማላዊ በከፍተኛ የሙቀት ማዕበል ልትመታ እንደምትችል ተነገረ

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በማላዊ የሙቀት መጠን እስከ 44 ዲግሪ ሴልሺየስ በመጨመር ከፍተኛ የሙቀት ማዕበል ሊያስከትል ስለሚችል ነዋሪዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።

ሙቀቱ የሰውነት ድርቀት ስለሚያስከትል ሰዎች አልኮል እና ሌሎች እንደ ቡናና ሻይ ያሉ አነቃቂ መጠጦችን ከመጠጣት እንዲቆጠቡም ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል።

የሀገሪቱ የአየር ሁኔታ ቢሮ እንዳመለከተው፤ በጥቅምት ወር ከፍተኛ ሙቀት የተለመደ ቢሆንም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ሙቀቱ የበለጠ እና ከባድ ሊሆን እንደሚችል ገልጿል።

ባለፈው የፈረንጆቹ ሐምሌ ወር የሰሜን አፍሪካ፣ የአውሮፓ፣ የአሜሪካ እና የሜክሲኮ አካባቢዎች ከፍተኛ በሆነ የሙቀት ማዕበል መመታታቸውን ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል።

ይህ የፈረንጆቹ 2023 እየተለቀቀ ካለው ሙቀትአምጪ ጋዝ (ካርበን) እና የኤልኒኖ የአየር ሁኔታ ክስተቶች ጋር ተዳምሮ እስካሁን ከተመዘገበው በተለየ እጅግ ሞቃታማ ዓመት ሊሆን እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የማላዊ የአየር ትንበያ ባለሙያ ዮቡ ካቺዋንዳ፤ የሙቀቱን መጨመር ተከትሎ ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና እክሎችን ለመከላከልም ነዋሪዎች የውሃ ጥም ባይሰማቸውም በቀን ውስጥ ብዙ ውሃ እንዲጠጡ መክረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ስስ ልብስ እንዲለብሱ፣ ከፍ ካለ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲቆጠቡ እና ቆዳቸውን ለመጠበቅም የፀሐይ ብርሃን መከላከያ ቅባት (ሰን ስክሪን) እንዲቀቡ አስገንዝበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.