Fana: At a Speed of Life!

አየር መንገዱ ከቦይንግ ኩባንያ እስከ ሰኔ ወር መጨረሻ የካሳ ክፍያ እንደሚጠብቅ አስታወቀ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 10 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቦይንግ ኩባንያ እስከ ሰኔ ወር መጨረሻ ድረስ የካሳ ክፍያ እንደሚጠብቅ አስታወቀ።
 
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም፥ አየር መንገዱ በቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኑ ላይ ለደረሰው አደጋ እስከ ሰኔ ወር መጨረሻ ድረስ ከኩባንያው ካሳ እንደሚጠብቅ ተናግረዋል።
 
አቶ ተወልደ ከሬውተርስ ጋር ባደረጉት ቆይታ አየር መንገዱ ቦይንግን በካሳ ክፍያው ዙሪያ ለውይይት እንደጋበዘው ጠቅሰው፥ ካሳው ቢሾፍቱ አቅራቢያ በተከሰከሰው ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ለደረሰው ጉዳት መሆኑን አንስተዋል።
 
ከዚህ ባለፈም አየር መንገዱ ከኩባንያው እንዲቀርቡለት ያዘዛቸውና በጊዜ ባልተረከባቸው አውሮፕላኖች ሳቢያ ያጣውን ገቢ ታሳቢ ያደረገ ይሆናልም ነው ያሉት አቶ ተወልደ።
 
ዋና ስራ አስፈጻሚው የካሳ ክፍያውን የበጀት አመቱ መዝጊያ በሆነው ሰኔ ወር መጨረሻ ድረስ እንደሚጠብቁም ነው የተናገሩት።
 
የካሳውን መጠን ያልጠቀሱት ዋና ስራ አስፈጻሚው ካሳው በገንዘብ አልያም በአውሮፕላን እቃ አቅርቦት መልክ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።
 
አቶ ተወልደ አያይዘውም አየር መንገዱ አሁን ላይ ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ በመንገደኞች ያጣውን ገቢ ለማካካስ 22 አውሮፕላኖቹን ለእቃ መጫኛነት በማዋል እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
 
የጭነት አውሮፕላኖች አገልግሎት የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ቁሳቁሶችን ለማቅረብ ተፈላጊነታቸው የጨመረ ሲሆን፥ አየር መንገዱም ከመንገደኞች ያጣውን ገቢ በዚህ ለማካከስ እየሰራ ነው ብለዋል።
 
አየር መንገዱ ከየካቲት እስከ ሚያዚያ ወር ድረስ 550 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ማጣቱንም ጠቁመዋል።
 
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ቦይንግ ኩባንያ ያለው ነገር ባይኖርም ፍትሃዊና ምክንያታዊ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ሌሎች አካላት ጋር በቅርበት እንደሚሰራ አስታውቋል።
 
ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነው ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ባለፈው አመት መጋቢት ወር ላይ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከተነሳ ከደቂቃዎች በኋላ መከስከሱ ይታወሳል።
 
#FBC
 
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.