Fana: At a Speed of Life!

3 ኢትዮጵያውያን የጣሊያኑ ኢኒ ዓለም አቀፍ ሽልማት አሸናፊ ሆኑ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሦስት ኢትዮጵያውያን “የአፍሪካ ወጣት ባለ ተሰጥዖዎች” በሚል ዘርፍ የ2023 የኢኒ ዓለምአቀፍ ሽልማት አሸናፊ መሆናቸው ተገለጸ፡፡

የሽልማቱ አሸናፊዎች ዔልሻዳይ ሙሉ ፈጠነ ከኬንያ ሞይ ዩኒቨርሲቲ፣ ፂዮን አያሌው ከበደ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ናትናዔል ጥላሁን ስንሻው ከአዲስ አበባ ሣይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ናቸው።

ከኢትዮጵያውያኑ በተጨማሪ ÷ ግሎሪያ አሞን ዱዱ የምትባል ደቡብ አፍሪካዊት ከደርባን ዩኒቨርሲቲ ሽልማቱን በዘርፉ ማሸነፏ በመረጃው ተመላክቷል፡፡

አሸናፊዎቹ የሦስት ዓመታት የዶክትሬት ትምህርታቸውን በጣሊያን ይከታተላሉ ተብሏል፡፡

የኢኒ 2023 የሽልማት መርሐ-ግብር ÷ የጣሊያኑ ፕሬዚዳንት ሰርጂዮ ማታሬላ በተገኙበት በኪውሪናል ቤተ-መንግሥት በዛሬው ዕለት ተካሂዷል፡፡

በመርሐ-ግብሩ ÷ የኢኒ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀ-መንበር ጁሴፔ ዛፋራና እና ዋና ሥራ አሥፈፃሚው ክላውዲዮ ዴስካልዚም መገኘታቸው ተጠቁሟል፡፡

ኩባንያው በዓለም አቀፍ ደረጃ በኃይል አቅርቦት ዘርፍ ፣ በዘላቂ የኃይል አማራጭ እንዲሁም በአካባቢ ጥበቃ ላይ ለሚሠሩ ምርጥ የጥናት እና ምርምር ሥራዎች ከፈረንጆቹ 2008 ጀምሮ ዕውቅና ሲሰጥ ቆይቷል፡፡

የኢኒ ሽልማት ከተጀመረበት ከፈረንጆቹ 2008 ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ከ11 ሺህ በላይ የጥናትና ምርምር ሥራ ማመልከቻዎች ለውድድር መቅረባቸውን የኩባንያው መረጃ ያመላክታል፡፡

ተቋሙ “የአፍሪካ ወጣት ባለ ተሰጥዖዎች” ከሚለው የሽልማት ዘርፍ በተጨማሪ የኃይል አቅርቦት ሽግግር ፣ የኃይል አቅርቦት ግንባር ቀደሞች ፣ በአካባቢ ጥበቃ ላይ የላቀ መፍትሄ አመላካቾች በሚሉት ዘርፎችም ዓለም አቀፍ ሽልማቶች ይሸልማል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.